ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሚልክያስ 2:11-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ይሁዳ አልታመነም፤ በእስራኤልና በኢየሩሳሌምም አስጸያፊ ነገር ተፈጽሞአል፤ ይሁዳ የባዕድ አምላክ ሴት ልጅ በማግባት እግዚአብሔር የሚወደውን መቅደስ አርክሶአል።

12. ይህን የሚያደርግ ማንኛውም ሰው ቢሆን፣ ለእግዚአብሔር ጸባኦት ቊርባን ቢያመጣም እንኳ፣ እግዚአብሔር ከያዕቆብ ድንኳን ያስወግደው።

13. ሌላው የምታደርጉት ነገር ደግሞ፣ የእግዚአብሔርን መሠዊያ በእንባ ታጥለቀልቃላችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ቊርባናችሁን ስለ ማይመለከትና በደስታም ከእጃችሁ ስለማይቀበል ታለቅሳላችሁ፤ ትጮኻ ላችሁም።

14. እናንተም፣ “ለምን ይህ ሆነ?” ብላችሁ ትጠይቃላችሁ። ይህ የሆነው የትዳር ጓደኛህን፣ አጋርህንና የቃል ኪዳን ሚስትህን፣ አታለሃታልና እግዚአብሔር በአንተና በወጣትነት ሚስትህ መካከል ላለው ቃል ኪዳን ምስክር ስለ ሆነ ነው።

15. እግዚአብሔር አንድ አላደረጋቸውምን? በሥጋም በመንፈስም የእርሱ ናቸው። ለምን አንድ አደረጋቸው? ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለውን ዘር ይፈልግ ስለ ነበር ነው። ስለዚህ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ከወጣትነት ሚስታችሁም ጋር ያላችሁን ታማኝነት አታጓድሉ።

16. “ፍችን እጠላለሁ” ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፤ ልብሱን በግፍ ድርጊት የሚሸፍነውንም ሰው እጠላለሁ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።ስለዚህ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ታማኝነታችሁም አይጓደል።

17. እግዚአብሔርን በቃላችሁ አታክታችሁታል።እናንተም፣ “ያታከትነው እንዴት ነው?” ትላላችሁ?“ክፉ የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነው፤ እርሱም በክፉዎች ደስ ይለዋል” ወይም “የፍትሕ አምላክ ወዴት ነው?” በማለታችሁ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሚልክያስ 2