ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሚልክያስ 2:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “አሁንም ካህናት ሆይ፤ ይህ ማስጠንቀቂያ ለእናንተ የተሰጠ ነው፤

2. ባትሰሙ፣ ልባችሁንም ስሜን ለማክበር ባታዘጋጁ፣ ርግማን እሰድባችኋለሁ፤ በረከታችሁንም ወደ መርገም እለውጠዋለሁ፤ ልታከብሩኝ ልባችሁን አላዘጋጃችሁምና’ ረግሜዋለሁ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

3. “ዘራችሁን እገሥጻለሁ፤ የመሥዋታችሁን ፋንድያ በፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፤ እናንተም ከእርሱ ጋር ትወገዳላችሁ፤

4. ከሌዊ ጋር የገባሁት ኪዳን ይጸና ዘንድ፣ ይህን ማስጠንቀቂያ የላክሁት እኔ መሆኔንም ታውቃላችሁ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

5. “ከእርሱ ጋር የገባሁት ኪዳን የሕይወትና የሰላም ኪዳን ነበር፤ እነርሱንም ሰጠሁት፤ ይህም ክብርን አመጣ፤ እርሱም አከበረኝ፤ ስሜንም በመፍራትም ጸና።

6. እውነተኛ ትምህርት በአፉ ነበር፤ ምንም ዐይነት የሐሰት ነገር በአንደበቱ አልተገኘም፤ ከእኔ ጋር በሰላምና በቅንነት ተራመደ፤ ብዙዎችንም ከኀጢአት መለሰ።

7. “ካህኑ የሁሉ ገዥ፣ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ስለ ሆነ ከንፈሮቹ ዕውቀትን ሊጠብቁ፣ ሰዎችም ከአንደበቱ ትምህርትን ሊፈልጉ ይገባል፤

8. እናንተ ግን ከመንገዱ ወጥታችኋል፤ በትምህርታችሁም ብዙዎች እንዲሰናከሉ አድርጋችኋል፤ የሌዊንም ኪዳን አፍርሳችኋል” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

9. “ስለዚህ በመንገዴ ስላልሄዳችሁና በትምህርታችሁም አድልዎ ስላደረጋችሁ፣ በሰዎች ሁሉ ፊት እንድትናቁና እንድትዋረዱ አድርጌአችኋለሁ።”

10. ሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለንምን? የፈጠረንስ አንድ አምላክ አይደለምን? ታዲያ እርስ በርሳችን ታማኝነት በማጒደል የአባቶቻችንን ኪዳን ለምን እናረክሳለን?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሚልክያስ 2