ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 89:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ስለ እግዚአብሔር ምሕረት ለዘለላለም እዘምራለሁ፤በአፌም ታማኝነትህን ከትውልድ እስከ ትውልድ እገልጻለሁ።

2. ምሕረትህን ለዘላለም እንደምትመሠርት፣ታማኝነትህንም በሰማይ እንደምታጸና እናገራለሁና።

3. አንተም እንዲህ ብለሃል፤ “ከመረጥሁት ጋር ኪዳን ገብቻለሁ፤ለባሪያዬ ለዳዊት ምያለሁ፤

4. ‘ዘርህን ለዘላለም እተክላለሁ፤ዙፋንህንም ከትውልድ እስከ ትውልድ አጸናለሁ።’ ” ሴላ

5. እግዚአብሔር ሆይ፤ ሰማያት ድንቅ ሥራህን፣ታማኝነትህንም በቅዱሳን ጉባኤ መካከል ያወድሳሉ፤

6. በላይ በሰማያት ከእግዚአብሔር ጋር ማን ሊስተካከል ይችላል?ከሰማያውያን ፍጥረታትስ መካከል ማን እግዚአብሔርን ይመስለዋል?

7. እግዚአብሔር በቅዱሳን ጉባኤ መካከል በጣም የሚፈራ፣በዙሪያውም ካሉት ሁሉ በላይ እጅግ የሚከበር ነው።

8. የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ኀያል ነህ፤ ታማኝነትህም ከብቦሃል።

9. የባሕርን ቍጣ ትቈጣጠራለህ፤ሞገዱም ሲነሣ ጸጥ ታደርገዋለህ።

10. አንተ ረዓብን የተሰየፈ ያህል አደቀቅኸው፤በብርቱ ክንድህም ጠላቶችህን በተንሃቸው።

11. ሰማያት የአንተ ናቸው፤ ምድርም የአንተ ናት፤ዓለምንና በውስጧ ያለውን ሁሉ አንተ መሠረትህ።

12. ሰሜንንና ደቡብን የፈጠርህ አንተ ነህ፤ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ሐሤት ያደርጋሉ።

13. አንተ ክንደ ብርቱ ነህ፤እጅህ ኀያል ናት፤ ቀኝ እጅህም ከፍ ከፍ ያለች ናት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 89