ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 79:2-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. የባሪያዎችህን ሬሳ ለሰማይ ወፎች፣የቅዱሳንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት፣ምግብ አድርገው ሰጡ።

3. ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ፣እንደ ውሃ አፈሰሱ፤የሚቀብራቸውም አልተገኘም።

4. እኛም ለጎረቤቶቻችን መዘባበቻ፣በዙሪያችንም ላሉት መሣቂያ መሣለቂያ ሆንን።

5. እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ እስከ መቼ ነው?የምትቈጣውስ ለዘላለም ነውን?ቅናትህስ እንደ እሳት ሲነድ ይኖራልን?

6. በማያውቁህ ሕዝቦች ላይ፣ስምህን በማይጠሩ፣መንግሥታት ላይ፣መዓትህን አፍስስ፤

7. ያዕቆብን በልተውታልና፤መኖሪያ ቦታውንም ባድማ አድርገዋል።

8. የአባቶቻችንን ኀጢአት በእኛ ላይ አትቍጠርብን፤ምሕረትህ ፈጥና ወደ እኛ ትምጣ፤በጭንቅ ላይ እንገኛለንና።

9. አዳኛችን የሆንህ አምላክ ሆይ፤ስለ ስምህ ክብር ብለህ እርዳን፤ስለ ስምህ ስትል፣ታደገን፤ ኀጢአታችንንም ይቅር በል።

10. ሕዝቦች፣ “አምላካቸው የት አለ?”ለምን ይበሉ?የፈሰሰውን የአገልጋዮችህን ደም በቀል፣ዐይናችን እያየ ሕዝቦች ይወቁት።

11. የእስረኞች ሰቈቃ በፊትህ ይድረስ፤በክንድህም ብርታት፣ሞት የተፈረደባቸውን አድን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 79