ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 78:7-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. እነርሱም በእግዚአብሔር ይታመናሉ፤ የእግዚአብሔርን ሥራ አይረሱም፤ትእዛዞቹንም ይጠብቃሉ።

8. ነገር ግን እንደ አባቶቻቸው፣እልከኞችና ዐመፀኞች፣ልቡን ያላቀና፣መንፈሱም በእግዚአብሔር የማይታመን ትውልድ አይሆኑም።

9. የኤፍሬም ልጆች የታጠቁ ቀስተኞች ቢሆኑም፣በጦርነት ቀን ወደ ኋላ ተመለሱ።

10. የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም፤ በሕጉም መሠረት ለመሄድ እንቢ አሉ።

11. እርሱ የሠራውን ሥራ፣ያሳያቸውንም ድንቅ ነገር ረሱ።

12. አባቶቻቸው በዐይናቸው እያዩ፣በግብፅ አገር፣ በጣኔዎስ ምድር ታምራት አደረገ።

13. ባሕሩን ከፍሎ አሻገራቸው፤ውሃውንም እንደ ክምር አቆመ።

14. ቀን በደመና መራቸው፤ሌሊቱንም ሁሉ በእሳት ብርሃን።

15. ዐለቱን በምድረ በዳ ሰነጠቀ፤እንደ ባሕር የበዛ ውሃ አጠጣቸው፤

16. ምንጭ ከቋጥኝ አፈለቀ፤ውሃን እንደ ወንዝ አወረደ።

17. እነርሱ ግን በምድረ በዳ በልዑል ላይ በማመፅ፣በእርሱ ላይ ኀጢአት መሥራታቸውን ቀጠሉ።

18. እጅግ የተመኙትን ምግብ በመጠየቅ፣እግዚአብሔርን በልባቸው ተፈታተኑት።

19. እንዲህም ብለው በእግዚአብሔር ላይ ተናገሩ፤“እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድ ማሰናዳት ይችላልን?

20. ዐለቱን ሲመታ፣ ውሃ ተንዶለዶለ፤ጅረቶችም ጐረፉ፤ታዲያ፣ እንጀራንም መስጠት ይችላል?ሥጋንስ ለሕዝቡ ሊያቀርብ ይችላል?”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 78