ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 78:35-51 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

35. እግዚአብሔር ዐለታቸው፣ልዑል አምላክ ቤዛቸው እንደሆነ አሰቡ።

36. ነገር ግን በአፋቸው ሸነገሉት፤በአንደበታቸው ዋሹት።

37. ልባቸው በእርሱ የጸና አልነበረም፤ለኪዳኑም ታማኞች አልነበሩም።

38. እርሱ ግን መሓሪ እንደ መሆኑ፣በደላቸውን ይቅር አለ፤አላጠፋቸውም፤ቊጣውን ብዙ ጊዜ ገታ፤መዓቱንም ሁሉ አላወረደም።

39. ወጥቶ የማይመለስ ነፋስ፣ሥጋ ለባሾች መሆናቸውን አሰበ።

40. በምድረ በዳ ስንት ጊዜ ዐመፁበት!በበረሓስ ምን ያህል አሳዘኑት!

41. ደግመው ደጋግመው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት፤የእስራኤልንም ቅዱስ አስቈጡት።

42. እነርሱን በዚያን ቀን ከጠላት የታደገበትን፣ያን ኀይሉን አላስታወሱም፤

43. በግብፅ ያደረገውን ታምራዊ ምልክት፣በጣኔዎስም በረሓ ያሳየውን ድንቅ ሥራ አላሰቡም።

44. ወንዞቻቸውን ወደ ደም ለወጠ፤ከጅረቶቻቸውም መጠጣት አልቻሉም።

45. የዝንብ ሰራዊት ሰደደባቸው፤ ነደፏቸውም፤ጓጒንቸርም ላከባቸው፤ ሰዎችንም አጠፉ።

46. አዝመራቸውን ለኵብኵባ፣ሰብላቸውንም ለአንበጣ ሰጠባቸው።

47. የወይን ተክላቸውን በበረዶ፣የበለስ ዛፋቸውንም በውርጭ አጠፋ።

48. ከብቶቻቸውን ለበረዶ፣የከብት መንጋቸውን ለመብረቅ እሳት ዳረገ።

49. ጽኑ ቍጣውን በላያቸው ሰደደ፤መዓቱን፣ የቅናቱን ቍጣናመቅሠፍቱን ላከባቸው፤አጥፊ የመላእክት ሰራዊትም ሰደደባቸው።

50. ለቊጣው መንገድ አዘጋጀ፤ነፍሳቸውንም ከሞት አላተረፈም፤ነገር ግን ሕይወታቸውን ለመቅሠፍት አሳልፎ ሰጠ።

51. የዐፍላ ጒልበታቸው መጀመሪያ የሆኑትን በካም ድንኳን፣በኵሮቻቸውንም ሁሉ በግብፅ ምድር ፈጀ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 78