ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 78:10-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም፤ በሕጉም መሠረት ለመሄድ እንቢ አሉ።

11. እርሱ የሠራውን ሥራ፣ያሳያቸውንም ድንቅ ነገር ረሱ።

12. አባቶቻቸው በዐይናቸው እያዩ፣በግብፅ አገር፣ በጣኔዎስ ምድር ታምራት አደረገ።

13. ባሕሩን ከፍሎ አሻገራቸው፤ውሃውንም እንደ ክምር አቆመ።

14. ቀን በደመና መራቸው፤ሌሊቱንም ሁሉ በእሳት ብርሃን።

15. ዐለቱን በምድረ በዳ ሰነጠቀ፤እንደ ባሕር የበዛ ውሃ አጠጣቸው፤

16. ምንጭ ከቋጥኝ አፈለቀ፤ውሃን እንደ ወንዝ አወረደ።

17. እነርሱ ግን በምድረ በዳ በልዑል ላይ በማመፅ፣በእርሱ ላይ ኀጢአት መሥራታቸውን ቀጠሉ።

18. እጅግ የተመኙትን ምግብ በመጠየቅ፣እግዚአብሔርን በልባቸው ተፈታተኑት።

19. እንዲህም ብለው በእግዚአብሔር ላይ ተናገሩ፤“እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድ ማሰናዳት ይችላልን?

20. ዐለቱን ሲመታ፣ ውሃ ተንዶለዶለ፤ጅረቶችም ጐረፉ፤ታዲያ፣ እንጀራንም መስጠት ይችላል?ሥጋንስ ለሕዝቡ ሊያቀርብ ይችላል?”

21. እግዚአብሔር ይህን ሲሰማ፣ እጅግ ተቈጣ፤በያዕቆብም ላይ እሳት ነደደ፤ቍጣውም በእስራኤል ላይ ተነሣ፤

22. በእግዚአብሔር አላመኑምና፤በእርሱም ማዳን አልታመኑም።

23. እርሱ ግን ከላይ ደመናትን አዘዘ፤የሰማይንም ደጆች ከፈተ፤

24. ይበሉም ዘንድ መና አዘነበላቸው፤የሰማይንም መብል ሰጣቸው።

25. ሰዎች የመላእክትን እንጀራ በሉ፤ጠግበው እስከሚተርፍ ድረስ ምግብ ላከላቸው።

26. የምሥራቁን ነፋስ ከሰማይ አስነሣ፤የደቡብንም ነፋስ በኀይሉ አመጣ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 78