ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 77:3-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. አምላክ ሆይ፤ አንተን ባሰብሁ ቍጥር ቃተትሁ፤ባወጣሁ ባወረድሁም መጠን መንፈሴ ዛለች። ሴላ

4. ዐይኖቼ እንዳይከደኑ ያዝሃቸው፤መናገር እስኪሳነኝ ድረስ ታወክሁ።

5. የድሮውን ዘመን አሰብሁ፤የጥንቶቹን ዓመታት አውጠነጠንሁ።

6. ዝማሬዬን በሌሊት አስታወስሁ፤ከልቤም ጋር ተጫወትሁ፤ መንፈሴም ተነቃቅቶ እንዲህ ሲል ጠየቀ፦

7. “ለመሆኑ፣ ጌታ ለዘላለም ይጥላልን?ከእንግዲህስ ከቶ በጎነትን አያሳይምን?

8. ምሕረቱስ ለዘላለም ጠፋን?የገባውስ ቃል እስከ ወዲያኛው ተሻረን?

9. እግዚአብሔር ቸርነቱን ዘነጋ?ወይስ ከቍጣው የተነሣ ርኅራኄውን ነፈገ?።” ሴላ

10. እኔም፣ “የልዑል ቀኝ እጅ እንደ ተለወጠ ማሰቤ፣ይህ ድካሜ ነው” አልሁ።

11. የእግዚአብሔርን ሥራ አስታውሳለሁ፤የጥንት ታምራትህን በእርግጥ አስታውሳለሁ፤

12. ሥራህን ሁሉ አሰላስላለሁ፤ድንቅ ሥራህን ሁሉ አውጠነጥናለሁ።

13. አምላክ ሆይ፤ መንገድህ ቅዱስ ነው፤እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው?

14. ታምራትን የምታደርግ አምላክ አንተ ነህ፤በሕዝቦችም መካከል ኀይልህን ትገልጣለህ።

15. የያዕቆብንና የዮሴፍን ልጆች፣ሕዝብህን በክንድህ ተቤዠሃቸው። ሴላ

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 77