ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 71:5-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ተስፋዬ፤ከልጅነቴም ጀምሮ መታመኛዬ ነህና።

6. ከተወለድሁ ጀምሮ በአንተ ተደገፍሁ፤ከእናቴ ማሕፀን ያወጣኸኝ አንተ ነህ፤አንተ የዘወትር ምስጋናዬ ነህ።

7. ብዙዎች እንደ ጒድ አዩኝ፤አንተ ግን ጽኑ አምባዬ ነህ።

8. ቀኑን ሙሉ ክብርህን ያወራ ዘንድ፣አፌ በምስጋናህ ተሞልቶአል።

9. በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፤ጒልበቴም ባለቀበት ጊዜ አትተወኝ።

10. ጠላቶቼ ተነጋግረውብኛልና፤ሕይወቴን ለማጥፋት የሚሹ በአንድ ላይ አሢረዋል፤

11. እነርሱም፣ “እግዚአብሔር ትቶታል፤የሚያስጥለው የለምና፣ ተከታትላችሁ ያዙት” አሉ።

12. አምላክ ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ፤አምላኬ ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን።

13. ባላንጣ የሆኑብኝ ይፈሩ፤ ይጥፉም፤ሊጐዱኝ የሚፈልጉ፣ንቀትንና ውርደትን ይከናነቡ።

14. እኔ ግን ሁል ጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፤በምስጋና ላይ ምስጋና አቀርብልሃለሁ።

15. አንደበቴ ስለ ጽድቅህ፣ቀኑን ሙሉ ስለ ማዳንህ ይናገራል፤ማቆሚያ ልኩንም አላውቅም።

16. መጥቼ የጌታ እግዚአብሔርን ብርቱ ሥራ ዐውጃለሁ፤የአንተን ጽድቅ ብቻ እናገራለሁ።

17. አምላክ ሆይ፤ አንተ ከልጅነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤እኔም እስከ ዛሬ ድረስ ድንቅ ሥራህን ዐውጃለሁ።

18. አምላክ ሆይ፤ ሳረጅና ስሸብትም አትተወኝ፤ክንድህን ለመጭው ትውልድ፣ኀይልህን ኋላ ለሚነሣ ሕዝብ ሁሉ፣እስከምገልጽ ድረስ።

19. አምላክ ሆይ፤ ጽድቅህ እስከ ሰማያት ይደርሳል፤አንተ ታላላቅ ነገሮችን አድርገሃል፤አምላክ ሆይ፤ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?

20. ብዙ መከራና ጭንቅ ብታሳየኝም፣ሕይወቴን እንደ ገና ታድሳለህ፤ከምድር ጥልቅም፣እንደ ገና ታወጣኛለህ።

21. ክብሬን ትጨምራለህ፤ተመልሰህም ታጽናናኛለህ

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 71