ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 71:13-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ባላንጣ የሆኑብኝ ይፈሩ፤ ይጥፉም፤ሊጐዱኝ የሚፈልጉ፣ንቀትንና ውርደትን ይከናነቡ።

14. እኔ ግን ሁል ጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፤በምስጋና ላይ ምስጋና አቀርብልሃለሁ።

15. አንደበቴ ስለ ጽድቅህ፣ቀኑን ሙሉ ስለ ማዳንህ ይናገራል፤ማቆሚያ ልኩንም አላውቅም።

16. መጥቼ የጌታ እግዚአብሔርን ብርቱ ሥራ ዐውጃለሁ፤የአንተን ጽድቅ ብቻ እናገራለሁ።

17. አምላክ ሆይ፤ አንተ ከልጅነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤እኔም እስከ ዛሬ ድረስ ድንቅ ሥራህን ዐውጃለሁ።

18. አምላክ ሆይ፤ ሳረጅና ስሸብትም አትተወኝ፤ክንድህን ለመጭው ትውልድ፣ኀይልህን ኋላ ለሚነሣ ሕዝብ ሁሉ፣እስከምገልጽ ድረስ።

19. አምላክ ሆይ፤ ጽድቅህ እስከ ሰማያት ይደርሳል፤አንተ ታላላቅ ነገሮችን አድርገሃል፤አምላክ ሆይ፤ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?

20. ብዙ መከራና ጭንቅ ብታሳየኝም፣ሕይወቴን እንደ ገና ታድሳለህ፤ከምድር ጥልቅም፣እንደ ገና ታወጣኛለህ።

21. ክብሬን ትጨምራለህ፤ተመልሰህም ታጽናናኛለህ

22. አምላኬ ሆይ፤ ስለ ታማኝነትህ፣በበገና አመሰግንሃለሁ፤የእስራኤል ቅዱስ ሆይ፤በመሰንቆ እዘምርልሃለሁ።

23. ዝማሬ በማቀርብልህ ጊዜ ከንፈሮቼ በደስታ ይሞላሉ፤አንተ የተቤዠሃትም ነፍሴ እልል ትላለች።

24. አንደበቴ ስለ ጽድቅህ፣ቀኑን ሙሉ ያወራል፤የእኔን መጐዳት የሚፈልጉ፣አፍረዋልና፤ ተዋርደዋልም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 71