ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 69:12-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. በቅጥሩ ደጅ ለሚቀመጡት የመነጋገሪያ ርእስ፣ለሰካራሞችም መዝፈኛ ሆንሁ።

13. እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ ግን በወደድኸው ሰዓት፣ወደ አንተ እጸልያለሁ፤አምላክ ሆይ፤ በታላቅ ምሕረትህ፣በማዳንህም እርግጠኝነት መልስልኝ።

14. ከረግረግ አውጣኝ፤እሰጥም ዘንድ አትተወኝ፤ከጥልቅ ውሃ፣ከእነዚያ ከሚጠሉኝ ታደገኝ።

15. ጐርፍ አያጥለቅልቀኝ፤ጥልቅ ውሃም አይዋጠኝ፤ጒድጓዱም ተደርምሶ አይዘጋብኝ።

16. እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ በጎ ናትና ስማኝ፤እንደ ርኅራኄም ብዛት መለስ በልልኝ።

17. ፊትህን ከባሪያህ አትሰውር፤ጭንቅ ውስጥ ነኝና ፈጥነህ መልስልኝ።

18. ወደ እኔ ቀርበህ ታደገኝ፤ስለ ጠላቶቼም ተቤዠኝ።

19. የደረሰብኝን ስድብ፣ ዕፍረትና ውርደት ታውቃለህ፤ጠላቶቼንም አንድ በአንድ ታውቃቸዋለህ።

20. ስድብ ልቤን ጐድቶታል፤ተስፋዬም ተሟጦአል፤አስተዛዛኝ ፈለግሁ፤ አላገኘሁምም፤አጽናኝም ፈለግሁ፤ አንድም አልነበረም።

21. ምግቤን ከሐሞት ቀላቀሉ፤ለጥማቴም ሆምጣጤ ሰጡኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 69