ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 68:4-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ለስሙም ተቀኙ፤በደመናት ላይ የሚሄደውን ከፍ አድርጉት፤ስሙ እግዚአብሔር በተባለው ፊት፣እጅግ ደስ ይበላችሁ።

5. እግዚአብሔር በተቀደሰ ማደሪያው፣ለድኻ አደጉ አባት፣ ለባልቴቲቱም ተሟጋች ነው።

6. እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤተ ሰብ መካከል ያኖራል፤እስረኞችን ነጻ አውጥቶ ያስፈነድቃል፤ዐመፀኞች ግን ምድረ በዳ ይኖራሉ።

7. እግዚአብሔር ሆይ፤ በሕዝብህ ፊት በወጣህ ጊዜ፣በምድረ በዳም በተጓዝህ ጊዜ፣ ሴላ

8. በሲና አምላክ፣ በእግዚአብሔር ፊት፣በእስራኤል አምላክ፣ በእግዚአብሔር ፊት፣ምድር ተንቀጠቀጠች፤ሰማያትም ዶፍ አወረዱ።

9. እግዚአብሔር ሆይ፣ በቂ ዝናብ አዘነብህ፤ክው ብሎ የደረቀውን ርስትህን አረሰረስህ።

10. መንጋህ መኖሪያው አደረጋት፤እግዚአብሔር ሆይ፤ ከበረከትህ ለድኾች ሰጠህ።

11. ጌታ እንዲህ ሲል ቃሉን አስተላለፈ፤ትእዛዙን የሚያውጁትም ብዙ ሰራዊት ናቸው፤

12. “የሰራዊት ነገሥታት ፈጥነው ይሸሻሉ፤በሰፈር የዋሉ ሴቶችም ምርኮን ተካፈሉ።

13. በበጎች በረት መካከል ብትገኙ እንኳ፣ከብር እንደ ተሠሩ የርግብ ክንፎች፣በቅጠልያ ወርቅ እንደ ተለበጡ ላባዎች ናችሁ።”

14. ሁሉን ቻዩ በዚያ የነበሩትን ነገሥታት በበተነ ጊዜ፣በሰልሞን እንደሚወርድ በረዶ አደረጋቸው።

15. አንተ ብርቱ ተራራ፣ የባሳን ተራራ ሆይ፤አንተ ባለ ብዙ ጫፍ ተራራ፣ የባሳን ተራራ፤

16. እናንተ ባለ ብዙ ጫፍ ተራሮች ሆይ፤እግዚአብሔር ሊኖርበት የመረጠውን ተራራ፣በእርግጥ እግዚአብሔር ለዘላለም የሚኖርበትን ተራራ ለምን በምቀኝነት ዐይን ታያላችሁ?

17. የእግዚአብሔር ሠረገላዎች እልፍ አእላፍ ናቸው፤ሺህ ጊዜም ሺህ ናቸው፤ጌታ ከሲና ወደ መቅደሱ ገባ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 68