ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 50:10-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. የዱር አራዊት ሁሉ፣በሺ ተራራዎች ላይ ያለውም እንስሳ የእኔ ነውና።

11. በየተራራው ያለውን ወፍ ሁሉ ዐውቃለሁ፤በሜዳ የሚገኘው ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ የእኔ ነው።

12. ብራብ ለአንተ አልነግርህም፤ዓለምና በውስጧ ያለውም ሁሉ የእኔ ነውና።

13. ለመሆኑ፣ እኔ የኰርማ ሥጋ እበላለሁን?የፍየልንስ ደም እጠጣለሁን?

14. ለእግዚአብሔር የምስጋና መሥዋዕት አቅርብ፤ለልዑልም ስእለትህን ስጥ።

15. በመከራ ጊዜ ወደ እኔ ጩህ፤አድንሃለሁ፤ አንተም ታከብረኛለህ።”

16. ክፉውን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይለዋል፤“ሕጌን ለማነብነብ፣ኪዳኔንም በአፍህ ለመናገር ምን መብት አለህ?

17. ተግሣጼን ትጠላለህና፤ቃሌንም ወደ ኋላህ ትጥላለህ።

18. ሌባውን ስታይ አብረኸው ነጐድህ፤ዕድል ፈንታህንም ከአመንዝሮች ጋር አደረግህ።

19. አፍህን ለክፋት አዋልህ፤አንደበትህም ሽንገላን ጐነጐነ።

20. ተቀምጠህ ወንድምህን አማኸው፤የእናትህንም ልጅ ስም አጐደፍህ።

21. ይህን አድርገህ ዝም አልሁ፤እንዳንተ የሆንሁ መሰለህ።አሁን ግን እገሥጽሃለሁ፣ፊት ለፊትም እወቅስሃለሁ።

22. “እናንተ እግዚአብሔርን የምትረሱ፤ ይህን ልብ በሉ፤አለበለዚያ ብትንትናችሁን አወጣለሁ፤የሚያድናችሁም የለም።

23. የምስጋናን መሥዋዕት የሚሠዋ ያከብረኛል፤መንገዱንም ቀና ለሚያደርግ፣የእግዚአብሔርን ማዳን አሳየዋለሁ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 50