ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 50:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኀያሉ አምላክ፣ እግዚአብሔር ተናገረ፤ከፀሓይ መውጫ እስከ ፀሓይ መግቢያ ድረስ ምድርን ጠራት።

2. ፍጹም ውብ ከሆነችው ከጽዮን፣እግዚአብሔር አበራ።

3. አምላካችን ይመጣል፤ ዝምም አይልም፤የሚባላ እሳት በፊቱ፣የሚያስፈራ ዐውሎ ነፋስም በዙሪያው አለ።

4. በሕዝቡ ይፈርድ ዘንድ፣በላይ ያለውን ሰማይንና ምድርን እንዲህ ብሎ ይጠራል፤

5. “በመሥዋዕት ከእኔ ጋር ኪዳን የገቡትን፣ቅዱሳኔን ወደ እኔ ሰብስቧቸው።”

6. ሰማያት ጽድቁን ያውጃሉ፤እግዚአብሔር ራሱ ፈራጅ ነውና። ሴላ

7. “ሕዝቤ ሆይ፤ ስማኝ፤ ልንገርህ፤እስራኤል ሆይ፤ በአንተ ላይ ልመስክር፤አምላክህ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

8. ስለ መሥዋዕትህ አልነቀፍሁህም፤የሚቃጠል መሥዋዕትህማ ሁል ጊዜ በፊቴ ነው።

9. እኔ ግን ኮርማህን ከበረት፣ፍየሎችህንም ከጒረኖ የምፈልግ አይደለሁም፤

10. የዱር አራዊት ሁሉ፣በሺ ተራራዎች ላይ ያለውም እንስሳ የእኔ ነውና።

11. በየተራራው ያለውን ወፍ ሁሉ ዐውቃለሁ፤በሜዳ የሚገኘው ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ የእኔ ነው።

12. ብራብ ለአንተ አልነግርህም፤ዓለምና በውስጧ ያለውም ሁሉ የእኔ ነውና።

13. ለመሆኑ፣ እኔ የኰርማ ሥጋ እበላለሁን?የፍየልንስ ደም እጠጣለሁን?

14. ለእግዚአብሔር የምስጋና መሥዋዕት አቅርብ፤ለልዑልም ስእለትህን ስጥ።

15. በመከራ ጊዜ ወደ እኔ ጩህ፤አድንሃለሁ፤ አንተም ታከብረኛለህ።”

16. ክፉውን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይለዋል፤“ሕጌን ለማነብነብ፣ኪዳኔንም በአፍህ ለመናገር ምን መብት አለህ?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 50