ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 45:7-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃን ጠላህ፤ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ፣ከጓደኞችህ ይልቅ አንተን የደስታ ዘይት ቀባህ።

8. ልብስህ ሁሉ በከርቤ፣ በአደስና በጥንጁት መዐዛ ያውዳል፤በዝኆን ጥርስ ከተዋቡ ቤተ መንግሥቶችም፣የበገናና የመሰንቆ ድምፅ ደስ ያሰኙሃል።

9. ከተከበሩት ሴቶችህ መካከል የነገሥታት ሴቶች ልጆች ይገኛሉ፤ንግሥቲቱም በኦፊር ወርቅ አጊጣ በቀኝህ ቆማለች።

10. ልጄ ሆይ፤ አድምጪ፤ አስተዉይ፤ ጆሮሽንም አዘንብይ፤ሕዝብሽንና የአባትሽን ቤት እርሺ።

11. ንጉሥ በውበትሽ ተማርኮአል፤ጌታሽ ነውና አክብሪው።

12. የጢሮስ ሴት ልጅ እጅ መንሻ ይዛ ትመጣለች፤ሀብታሞችም ደጅ ይጠኑሻል።

13. የንጉሥ ልጅ ከላይ እስከ ታች ተሸልማ እልፍኟ ውስጥ አለች፤ልብሷም ወርቀ ዘቦ ነው።

14. በጥልፍ ሥራ ባጌጠ ልብስ ወደ ንጉሥ ትወሰዳለች፤ደናግል ጓደኞቿም ተከትለዋት፣ወደ አንተ ይመጣሉ።

15. በደስታና በሐሤት ወደ ውስጥ ይመሯቸዋል፤ወደ ንጉሡም ቤተ መንግሥት ይገባሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 45