ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 44:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. አምላክ ሆይ፤ በጆሮአችን ሰምተናል፤አባቶቻችን በቀድሞ ዘመን፣እነርሱ በነበሩበት ዘመን፣ያደረግኸውን ነግረውናል።

2. ሕዝቦችን በእጅህ አሳደህ አወጣሃቸው፤አባቶቻችንን ግን ተከልሃቸው፤ሕዝቦችን አደቀቅህ፤አባቶቻችንን ግን ነጻ አወጣሃቸው።

3. ምድሪቱን የወረሱት በሰይፋቸው አልነበረም፤ድልንም የተጐናጸፉት በክንዳቸው አይደለም፤አንተ ወደሃቸዋልና ቀኝ እጅህ፣ክንድህና የፊትህ ብርሃን ይህን አደረገ።

4. እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ንጉሤ ነህ፤ያዕቆብም ድል እንዲያደርግ የወሰንህ አንተ ነህ።

5. በአንተ ጠላቶቻችን በመጡበት እንዲመለሱ እናደርጋለን፤በስምህም ባላጋራዎቻችንን ከእግራችን በታች እንረግጣለን።

6. በቀስቴ አልተማመንም፤ሰይፌም አያስጥለኝም።

7. አንተ ግን በጠላቶቻችን ላይ ድልን ትሰጠናለህ፤ባላንጣዎቻችንንም ታሳፍራለህ።

8. ዘወትር በእግዚአብሔር እንመካለን፤ስምህንም ለዘላለም እንወድሳለን። ሴላ

9. አሁን ግን እነሆ ትተኸናል፤ አሳፍረኸናልም፤ከሰራዊታችንም ጋር አትወጣም።

10. ከጠላት ፊት እንድናፈገፍግ አደረግኸን፤ባላንጣዎቻችንም ዘረፉን።

11. እንደሚታረዱ በጎች አደረግኸን፤በሕዝቦችም መካከል በተንኸን።

12. ሕዝብህን በርካሽ ዋጋ ሸጥኸው፤ከሽያጩም ያገኘኸው ትርፍ የለም።

13. ለጎረቤቶቻችን ስድብ፣በዙሪያችን ላሉትም መሣቂያና መዘበቻ አደረግኸን።

14. በሕዝቦች ዘንድ መተረቻ፣በሰዎች መካከል በንቀት ራስ መነቅነቂያ አደረግኸን።

15. ውርደቴ ቀኑን ሙሉ በፊቴ ነው፤ፊቴም ዕፍረትን ተከናንቦአል።

16. ይህም ከሚዘልፍና ከሚያላግጥ ሰው ድምፅ የተነሣ፣ከጠላትና ከተበቃይ ሁኔታ የተነሣ ነው።

17. አንተን ሳንረሳ፣ለኪዳንህም ታማኝነታችንን ሳናጓድል፣ይህ ሁሉ ደረሰብን።

18. ልባችን ወደ ኋላ አላለም፤እግራችንም ከመንገድህ አልወጣም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 44