ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 40:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት፤እርሱም ዘንበል አለልኝ፤ ጩኸቴንም ሰማ።

2. ከሚውጥ ጒድጓድ፣ከሚያዘቅጥ ማጥ አወጣኝ፤እግሮቼን በዐለት ላይ አቆመ፤አካሄዴንም አጸና።

3. ለአምላካችን የሚሆን ውዳሴ፣አዲስ ዝማሬን በአፌ ላይ አኖረ፤ብዙዎች ያያሉ፤ ይፈራሉም፤ በእግዚአብሔር ይታመናሉ።

4. እግዚአብሔርን መታመኛው ያደረገ፣ወደ ትዕቢተኞች የማይመለከት፣የሐሰት አማልክትን ወደሚከተሉት የማያይ፣ሰው ብፁዕ ነው።

5. እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤አንተ ያደረግኸው ድንቅ ነገር ብዙ ነው፤ለእኛ ያቀድኸውን፣ሊዘረዝርልህ የሚችል ማንም የለም፤ላውራው ልናገረው ብል፣ስፍር ቍጥር አይኖረውም።

6. መሥዋዕትንና ቊርባንን አልፈለግህም፤ጆሮቼን ግን ከፈትህ፤የሚቃጠል መሥዋዕትን፣የኀጢአትንም መሥዋዕት አልሻህም።

7. እኔም እንዲህ አልሁ፤ “እነሆ፤ መጥቻለሁ፤ስለ እኔ በመጽሐፍ ተጽፎአል፤

8. አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 40