ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 35:12-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. በበጎ ፈንታ ክፉ መለሱልኝ፤ነፍሴንም ብቸኛ አደረጓት።

13. እኔ ግን እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፤ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፤ጸሎቴም መልስ አጥቶ ወደ ጒያዬ ተመለሰ።

14. ለወዳጄ ወይም ለወንድሜ እንደማደርግ፣እየተንቈራጠጥሁ አለቀስሁ፤ለእናቴም እንደማለቅስ፣በሐዘን ዐንገቴን ደፋሁ።

15. እነርሱ ግን እኔ ስሰናከል በእልልታ ተሰበሰቡ፤ግፈኞች በድንገት ተሰበሰቡብኝ፤ያለ ዕረፍትም ቦጫጨቁኝ።

16. እንደ ምናምንቴዎች አፌዙብኝ፤ጥርሳቸውንም አፋጩብኝ።

17. ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ ዝም ብለህ ታያለህ?ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው፣ብርቅ ሕይወቴን ከአንበሶች ታደጋት።

18. በታላቅ ጉባኤ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበትም አወድስሃለሁ።

19. ከምድር ተነሥተው ጠላቶቼ የሆኑት፣በላዬ ደስ አይበላቸው፤እንዲያው የሚጠሉኝ፣በዐይናቸው አይጣቀሱብኝ።

20. የሰላም ንግግር ከአፋቸው አይወጣም፤ዳሩ ግን በምድሪቱ በጸጥታ በሚኖሩት ላይ፣ነገር ይሸርባሉ።

21. አፋቸውን አስፍተው ከፈቱብኝ፤“ዕሠይ! ዕሠይ! በዐይናችን አየነው” አሉ።

22. እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን አይተሃልና ዝም አትበል፤ጌታ ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ።

23. አምላኬ፣ ጌታዬ፤ ለእኔ ለመሟገት ተነሥ!ልትከራከርልኝም ተንቀሳቀስ።

24. እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ በጽድቅህ ፍረድልኝ፤በእኔም ላይ ደስ አይበላቸው።

25. በልባቸው፣ “ዕሠይ! ያሰብነው ተሳካ!ዋጥ አደረግነውም” አይበሉ።

26. በጭንቀቴ ደስ የሚላቸው፣ይፈሩ፤ ግራም ይጋቡ፤በእኔ ላይ ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ፣ዕፍረትንና ውርደትን ይከናነቡ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 35