ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 31:4-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. አንተ መጠጊያዬ ነህና፣በስውር ከተዘረጋብኝ ወጥመድ አውጣኝ።

5. መንፈሴን በእጅህ ዐደራ እሰጣለሁ፤ እግዚአብሔር የእውነት አምላክ ሆይ፤አንተ ተቤዠኝ።

6. ለከንቱ ጣዖታት ስፍራ የሚሰጡትን ጠላሁ፤ነገር ግን በእግዚአብሔር ታመንሁ።

7. በምሕረትህ ደስ እሰኛለሁ፤ ሐሤትም አደርጋለሁ፤መከራዬን አይተሃልና፤የነፍሴንም ጭንቀት ዐውቀሃል።

8. ለጠላት አሳልፈህ አልሰጠኸኝም፤ነገር ግን እግሮቼን ሰፊ ቦታ ላይ አቆምሃቸው።

9. እግዚአብሔር ሆይ፤ በመከራ ውስጥ ነኝና ማረኝ፤ዐይኖቼ በሐዘን ደክመዋል፤ነፍስና ሥጋዬም ዝለዋል።

10. ሕይወቴ በመጨነቅ፣ዕድሜዬም በመቃተት ዐለቀ፤ከመከራዬ የተነሣ ጒልበት ከዳኝ፤ዐጥንቴም በውስጤ ሟሟ።

11. ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ፣ለጎረቤቶቼ መዘባበቻ፣ለወዳጆቼ መሣለቂያ ሆኛለሁ፤መንገድ ላይ የሚያገኙኝም ይሸሹኛል።

12. እንደ ሞተ ሰው ተረሳሁ፤እንደ ተሰበረ የሸክላ ዕቃም ተቈጠርሁ።

13. የብዙ ሰዎችን ሹክሹክታ እሰማለሁና፤ዙሪያው ሁሉ ሽብር አለ፤በእኔ ላይ ባሤሩ ጊዜ፣ሕይወቴን ለማጥፋት ዶለቱ።

14. እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ ግን በአንተ እታመናለሁ፤“አንተ አምላኬ ነህ” እልሃለሁም።

15. ዘመኔ ያለው በእጅህ ነው፤ከጠላቶቼ እጅ ታደገኝ፤ከሚያሳድዱኝም አድነኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 31