ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 31:12-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. እንደ ሞተ ሰው ተረሳሁ፤እንደ ተሰበረ የሸክላ ዕቃም ተቈጠርሁ።

13. የብዙ ሰዎችን ሹክሹክታ እሰማለሁና፤ዙሪያው ሁሉ ሽብር አለ፤በእኔ ላይ ባሤሩ ጊዜ፣ሕይወቴን ለማጥፋት ዶለቱ።

14. እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ ግን በአንተ እታመናለሁ፤“አንተ አምላኬ ነህ” እልሃለሁም።

15. ዘመኔ ያለው በእጅህ ነው፤ከጠላቶቼ እጅ ታደገኝ፤ከሚያሳድዱኝም አድነኝ።

16. ፊትህን በአገልጋይህ ላይ አብራ፤በምሕረትህም አድነኝ።

17. እግዚአብሔር ሆይ፤ወደ አንተ እጮኻለሁና አልፈር፤ክፉዎች ግን ይፈሩ፤ሲኦል ገብተውም ጸጥ ይበሉ።

18. በጻድቁ ላይ በእብሪት የሚናገሩ፣ትዕቢትንና ንቀትን የተሞሉ፣ዋሾ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ።

19. በሰዎች ልጆች ፊት፣ለሚፈሩህ ያስቀመጥሃት፣መጠጊያ ላደረጉህም ያዘጋጀሃት፣በጎነትህ ምንኛ በዛች!

20. ከሰዎች ሤራ፣በማደሪያህ ውስጥ ትሸሽጋቸዋለህ፤ከአንደበት ጭቅጭቅም፣በድንኳንህ ውስጥ ትከልላቸዋለህ።

21. በተከበበች ከተማ ውስጥ፣የሚያስደንቅ ምሕረቱን ያሳየኝ፣ እግዚአብሔር ይባረክ።

22. እኔ በደነገጥሁ ጊዜ፣“ከዐይንህ ፊት ተወግጃለሁ” አልሁ፤አንተ ግን ወደ አንተ ስጮኽ፣የልመናዬን ቃል ሰማህ።

23. እናንተ ቅዱሳኑ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ውደዱት! እግዚአብሔር ታማኞችን ይጠብቃል፤ትዕቢተኞችን ግን ፈጽሞ ይበቀላቸዋል።

24. እግዚአብሔርን ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ፤በርቱ፤ ልባችሁም ይጽና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 31