ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 140:5-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ትዕቢተኞች ወጥመድ በስውር አስቀመጡብኝ፤የመረባቸውን ገመድ ዘረጉብኝ፤በመንገዴም ላይ አሽክላ አኖሩ። ሴላ

6. እግዚአብሔር ሆይ፤ “አንተ አምላኬ ነህ” እልሃለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የልመና ጩኸቴን ስማ።

7. ብርቱ አዳኝ የሆንህ፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤በጦርነት ዕለት የራስ ቍር ሆንኸኝ።

8. እግዚአብሔር ሆይ፤ የክፉዎች ምኞት አይፈጸም፤በትዕቢትም እንዳይኵራሩ፣ዕቅዳቸው አይሳካ። ሴላ

9. ዙሪያዬን የከበቡኝ ሰዎች ራስ፣የከንፈራቸው መዘዝ ይጠምጠምበት።

10. የእሳት ፍም በላያቸው ይውረድ፤ዳግመኛም እንዳይነሡ ወደ እሳት ይጣሉ፤ማጥ ወዳለበት ጒድጓድ ይውደቁ።

11. ምላሰኛ በምድሪቱ ጸንቶ አይኑር፤ዐመፀኛውን ሰው ክፋት አሳዶ ያጥፋው።

12. እግዚአብሔር ለድኻ ፍትሕን እንደሚያስከብር፣ለችግረኛውም ትክክለኛ ፍርድን እንደሚሰጥ ዐውቃለሁ።

13. ጻድቃን በእውነት ስምህን ያመሰግናሉ፤ቅኖችም በፊትህ ይኖራሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 140