ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 119:54-73 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

54. በእንግድነቴ አገር፣ሥርዐትህ መዝሙሬ ናት።

55. እግዚአብሔር ሆይ፤ ስምህን በሌሊት ዐስባለሁ፤ሕግህንም እጠብቃለሁ።

56. ሥርዐትህን እከተላለሁ፤ይህችም ተግባሬ ሆነች።

57. እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ቃልህን ለመታዘዝ ቈርጫለሁ።

58. በፍጹም ልቤ ፊትህን ፈለግሁ፤እንደ ቃልህ ቸርነትህን አሳየኝ።

59. መንገዴን ቃኘሁ፤አካሄዴንም ወደ ምስክርህ አቀናሁ።

60. ትእዛዝህን ለመጠበቅ፣ቸኰልሁ፤ አልዘገየሁምም።

61. የክፉዎች ገመድ ተተበተበብኝ፤ እኔ ግን ሕግህን አልረሳሁም።

62. ስለ ጻድቅ ሥርዐትህ፣በእኩለ ሌሊት ላመሰግንህ እነሣለሁ።

63. እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፣ሥርዐትህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ።

64. እግዚአብሔር ሆይ፤ ምድር በምሕረትህ ተሞላች፤ሥርዐትህን አስተምረኝ።

65. እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ፣ለአገልጋይህ በጎ ውለሃል።

66. በትእዛዛትህ አምናለሁና፣ በጎ ማስተዋልንና ዕውቀትንአስተምረኝ።

67. እንዲያው ሳይቸግረኝ መንገድ ስቼ ሄድሁ፤አሁን ግን ቃልህን እጠብቃለሁ።

68. አንተ መልካም ነህ፤ የምታደርገው መልካም ነው፤እንግዲህ ሥርዐትህን አስተምረኝ።

69. እብሪተኞች ስሜን በሐሰት አጠፉ፤እኔ ግን ትእዛዝህን በፍጹም ልብ እጠብቃለሁ።

70. ልባቸው የሠባና የደነደነ ነው፤እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል።

71. ሥርዐትህን እማር ዘንድ፣በመከራ ውስጥ ማለፌ መልካም ሆነልኝ።

72. ከአእላፋት ብርና ወርቅ ይልቅ፣ከአፍህ የሚወጣው ሕግ ይሻለኛል።

73. እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ትእዛዛትህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 119