ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 112:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን የሚፈራ፣በትእዛዙም እጅግ ደስ የሚሰኝ የተባረከ ነው።

2. ዘሩ በምድር ላይ ኀያል ይሆናል፤የቅኖች ትውልድ ትባረካለች።

3. ሀብትና ብልጽግና በቤቱ ይሞላል፤ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል።

4. ቸር፣ ርኅሩኅና ጻድቅ እንደ መሆኑ፣ለቅን ሰው በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይወጣለታል።

5. ለጋስና ያለ ማንገራገር የሚያበድር፣ሥራውንም በትክክል የሚያከናውን ሰው መልካም ይሆንለታል፤

6. ለዘላለም ከስፍራው አይናወጥምና፤ጻድቅ ሰው ሲታወስ ይኖራል።

7. ክፉ ወሬ አያሸብረውም፤ልቡ እግዚአብሔርን በመተማመን የጸና ነው።

8. ልቡ የጸና ነው፤ አይፈራምም፤በመጨረሻም የጠላቶቹን ውድቀት ያያል።

9. በልግስና ለድኾች ሰጠ፤ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል፤ቀንዱም በክብር ከፍ ከፍ ይላል።

10. ክፉ ሰው ይህን በማየት ይበሳጫል፤ጥርሱን ያፋጫል፤ እየመነመነም ይጠፋል፤የክፉዎችም ምኞት ትጠፋለች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 112