ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 105:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤ሥራውንም በሕዝቦች መካከል ግለጡ።

2. ተቀኙለት፤ ዘምሩለት፤ድንቅ ሥራዎቹንም ሁሉ ተናገሩ።

3. በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚሹት ልባቸው ደስ ይበለው።

4. እግዚአብሔርንና ብርታቱን ፈልጉ፤ፊቱንም ዘወትር ፈልጉ።

5. ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎች፣ታምራቱንና ከአፉ የወጣውን ፍርድ አስቡ፤

6. እናንተ የአገልጋዩ የአብርሃም ዘሮች፣ለራሱም የመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ አስታውሱ።

7. እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ፍርዱም በምድር ሁሉ ላይ ነው።

8. ኪዳኑን ለዘላለም፣ያዘዘውንም ቃል እስከ ሺህ ትውልድ ያስታውሳል።

9. ከአብርሃም ጋር ያደረገውን ኪዳን፣ለይስሐቅም በመሐላ የተሰጠውን ተስፋ አይረሳም።

10. ይህንም ለያዕቆብ ሥርዐት አድርጎ፣ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን አድርጎ አጸናለት፤

11. እንዲህም አለ፤ “የርስትህ ድርሻ አድርጌ፣የከነዓንን ምድር እሰጥሃለሁ።”

12. በቍጥር አነስተኞች ሆነው ሳሉ፣እጅግ ጥቂትና ባይተዋሮች ሳሉ፣

13. ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ሲንከራተቱ፣ከአንዱ መንግሥት ወደ ሌላው ሲቅበዘበዙ፣

14. ማንም ግፍ እንዲፈጽምባቸው አልፈቀደም፤ስለ እነርሱም ነገሥታትን እንዲህ ሲል ገሠጸ፤

15. “የቀባኋቸውን አትንኩ፤በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ።”

16. በምድሪቱ ላይ ራብን ጠራ፤የምግብንም አቅርቦት ሁሉ አቋረጠ፤

17. በባርነት የተሸጠውን ሰው፣ዮሴፍን ከእነርሱ አስቀድሞ ላከ።

18. እግሮቹ በእግር ብረት ተላላጡ፤በዐንገቱም የብረት ማነቆ ገባ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 105