ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መክብብ 7:9-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. የሞኞች ቊጣ በዕቅፋቸው ውስጥ ስለ ሆነ፣በመንፈስህ ለቊጣ አትቸኵል።

10. አንተም፣ “ከእነዚህ ቀናት የቀድሞዎቹ ለምን ተሻሉ?” አትበል፤እንዲህ ያሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ጠቢብነት አይደለምና።

11. ጥበብ እንደ ርስት መልካም ነገር ነው፤ጠቃሚነቱም ፀሓይን ለሚያዩ ሰዎች ነው።

12. ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደሆነ ሁሉ፣ጥበብም ጥላ ከለላ ነው፤የዕውቀት ብልጫዋ ግን፣ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው።

13. እግዚአብሔር ያደረገውን ተመልከት፤እርሱ ያጣመመውን፣ማን ሊያቃናው ይችላል?

14. ጊዜው መልካም ሲሆን፣ ደስ ይበልህ፤ጊዜው ክፉ ሲሆን ግን ይህን አስብ፤እግዚአብሔር አንዱን እንዳደረገ፣ሌላውንም አድርጎአል፤ስለዚህ ሰው ስለ ወደ ፊት ሁኔታው፣ምንም ሊያውቅ አይችልም።

15. በዚህ ከንቱ በሆነው ሕይወቴ እነዚህን ሁለቱን ነገሮች አይቻለሁ፤ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ፣ኀጥእም በክፋቱ ዕድሜው ሲረዝም።

16. እጅግ ጻድቅ፣እጅግም ጠቢብ አትሁን፤ራስህን ለምን ታጠፋለህ?

17. እጅግ ክፉ አትሁን፤ሞኝም አትሁን፤ለምንስ ያለ ቀንህ ትሞታለህ?

18. አንዱን ይዞ ሌላውንም አለመልቀቅ መልካም ነው፤እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰውጽንፈኝነትን ያስወግዳል።

19. በአንድ ከተማ ካሉ ዐሥር ገዦች ይልቅ፣ጥበብ ጠቢቡን ሰው ኀያል ታደርገዋለች።

20. ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኀጢአት የማይሠራ፣ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም።

21. የሚነገረውን ቃል ሁሉ ለማዳመጥ አትሞክር፤አለበለዚያ አገልጋይህ ሲረግምህ ትሰማ ይሆናል፤

22. ብዙ ጊዜ አንተ ራስህ፣ሌሎችን እንደረገምህ ልብህ ያውቃልና።

23. እኔም ይህን ሁሉ በጥበብ ፈትኜ፣“ጠቢብ ለመሆን ቈርጫለሁ” አልሁ፤ይህ ግን ከእኔ የራቀ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መክብብ 7