ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መክብብ 7:3-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ሐዘን ከሣቅ ይሻላል፤ያዘነ ፊት ለልብ መልካም ነውና።

4. የጠቢባን ልብ በሐዘን ቤት ነው፤የሞኞች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው።

5. የሞኞችን መዝሙር ከመስማት፣የጠቢባንን ሰዎች ተግሣጽ መስማት ይሻላል።

6. የሰነፎች ሣቅ፣ከድስት ሥር እንደሚንጣጣ የእሾኽ ማገዶ ነው፤ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።

7. ግፍ ጠቢብን ሞኝ ያደርጋል፤ጒቦም ልብን ያበላሻል።

8. የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል፤ትዕግሥተኛም ከትዕቢተኛ ይሻላል፤

9. የሞኞች ቊጣ በዕቅፋቸው ውስጥ ስለ ሆነ፣በመንፈስህ ለቊጣ አትቸኵል።

10. አንተም፣ “ከእነዚህ ቀናት የቀድሞዎቹ ለምን ተሻሉ?” አትበል፤እንዲህ ያሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ጠቢብነት አይደለምና።

11. ጥበብ እንደ ርስት መልካም ነገር ነው፤ጠቃሚነቱም ፀሓይን ለሚያዩ ሰዎች ነው።

12. ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደሆነ ሁሉ፣ጥበብም ጥላ ከለላ ነው፤የዕውቀት ብልጫዋ ግን፣ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው።

13. እግዚአብሔር ያደረገውን ተመልከት፤እርሱ ያጣመመውን፣ማን ሊያቃናው ይችላል?

14. ጊዜው መልካም ሲሆን፣ ደስ ይበልህ፤ጊዜው ክፉ ሲሆን ግን ይህን አስብ፤እግዚአብሔር አንዱን እንዳደረገ፣ሌላውንም አድርጎአል፤ስለዚህ ሰው ስለ ወደ ፊት ሁኔታው፣ምንም ሊያውቅ አይችልም።

15. በዚህ ከንቱ በሆነው ሕይወቴ እነዚህን ሁለቱን ነገሮች አይቻለሁ፤ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ፣ኀጥእም በክፋቱ ዕድሜው ሲረዝም።

16. እጅግ ጻድቅ፣እጅግም ጠቢብ አትሁን፤ራስህን ለምን ታጠፋለህ?

17. እጅግ ክፉ አትሁን፤ሞኝም አትሁን፤ለምንስ ያለ ቀንህ ትሞታለህ?

18. አንዱን ይዞ ሌላውንም አለመልቀቅ መልካም ነው፤እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰውጽንፈኝነትን ያስወግዳል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መክብብ 7