ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መክብብ 5 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔርን ፍራ

1. ወደ እግዚአብሔር ቤት ስትሄድ እግርህን ጠብቅ። ለመስማት መቅረብ የሰነፎችን መሥዋዕት ከማቅረብ ይበልጣል፤ እነርሱ ክፉ እንደሚሠሩ አያውቁምና።

2. በአፍህ አትፍጠን፤በእግዚአብሔርም ፊት ማንኛውንም ነገር ለመናገር፣በልብህ አትቸኵል፤እግዚአብሔር በሰማይ፣አንተ ደግሞ በምድር ነህ፤ስለዚህ ቃልህ ጥቂት ይሁን።

3. በሥራ ብዛት ሕልም እንደሚታይ፣ብዙ ቃል ባለበትም የሞኝ ንግግር ይገለጣል።

4. ለእግዚአብሔር ስእለትን በተሳልህ ጊዜ ለመፈጸም አትዘግይ፤ በሰነፎች ደስ አይለውምና፤ ስእለትህን ፈጽም።

5. ስእለት ተስሎ ካለመፈጸም፣ አለመሳል ይሻላል።

6. አንደበትህ ወደ ኀጢአት እንዲመራህ አትፍቀድ፤ ለቤተ መቅደስ መልእክተኛም፣ “የተሳልሁት በስሕተት ነበር” አትበል። እግዚአብሔር በተናገርኸው ተቈጥቶ የእጅህን ሥራ ለምን ያጥፋ?

7. ብዙ ሕልምና ብዙ ቃል ከንቱ ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን ፍራ።

ባለጠግነት ከንቱ ነው

8. በአገር ውስጥ ድኻ ተጨቍኖ፣ ፍትሕ ተጓድሎ፣ መብትም ተረግጦ ብታይ፣ እንደነዚህ ባሉ ነገሮች አትደነቅ፤ ምክንያቱም አንዱን አለቃ የበላዩ ይመለከተዋል፤ በእነዚህ በሁለቱም ላይ ሌሎች ከፍ ያሉ አሉ።

9. ከምድሩ የሚገኘው ትርፍ ለሁሉም ነው፤ ንጉሡም ራሱ የሚጠቀመው ከዕርሻ ነው።

10. ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም፤ይህም ከንቱ ነው።

11. ሀብት በበዛ ቊጥር፣ተጠቃሚውም ይበዛል፤በዐይኑ ብቻ ከማየት በቀርታዲያ፣ ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል?

12. ጥቂትም ይሁን ብዙ ቢበላ፣የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤የሀብታም ሰው ብልጽግና ግንእንቅልፍ ይነሣዋል።

13. ከፀሓይ በታች የሚያሳዝን ክፉ ነገር አየሁ፦ይህም ለባለቤቱ ጒዳት የተከማቸ ሀብት፣

14. ወይም በአንድ መጥፎ አጋጣሚ የጠፋ ብልጽግና ነው፤ልጅ ሲወልድም፣ለእርሱ የሚያስቀርለት ምንም ነገር አይኖርም።

15. ሰው ከእናቱ ማሕፀን ዕራቊቱን ይወለዳል፤እንደ መጣው እንዲሁ ይመለሳል።ከለፋበትም ነገር፣አንድም እንኳ በእጁ ይዞ ሊሄድ አይችልም።

16. ይህ ደግሞ እጅግ ክፉ ነገር ነው፤ሰው እንደ መጣ እንዲሁ ይሄዳል፤የሚደክመው ለነፋስ ስለ ሆነ፣ትርፉ ምንድ ነው?

17. በብዙ ጭንቀት፣ መከራና ብስጭት፣ዘመኑን ሁሉ በጨለማ ውስጥ ይበላል።

18. የሰው ዕጣው ይህ ስለ ሆነ፣ እግዚአብሔር በሰጠው በጥቂት ዘመኑ ከፀሓይ በታች በሚደክምበት ነገር ርካታን ያገኝ ዘንድ፣ መብላቱና መጠጣቱም መልካምና ተገቢ መሆኑን ተገነዘብሁ።

19. እግዚአብሔር ለሰው ባለጠግነትና ሀብት መስጠቱ፣ እንዲደሰትበትም ማስቻሉ፣ ዕጣውን እንዲቀበልና በሥራውም እንዲደሰት ማድረጉ፣ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።

20. እግዚአብሔር የልብ ደስታ ስለሚሰጠውም በሕይወቱ ዘመን ያሉትን ቀናት እምብዛም አያስባቸውም።