ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መክብብ 12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የጭንቀት ጊዜ ሳይመጣ፣“ደስ አያሰኙኝም”የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ፣በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ።

2. ፀሓይና ብርሃን፣ጨረቃና ከዋክብት ሳይጨልሙ፣ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ፣

3. ቤት ጠባቂዎች ሲርዱ፣ብርቱዎች ሲጐብጡ፣ጥቂት በመሆናቸው ፈጪታዎች ሲያቆሙ፣በመስኮት የሚያዩትም ሲፈዙ፣

4. ወደ አደባባይ የሚያወጡ በሮች ሲዘጉ፣ወፍጮ ሟልጦ ድምፁ ሲላሽ፣ሰው በወፍ ድምፅ ሲነሣ፣ዝማሬው ሁሉ ሲዳከም፤

5. ዳገት መውጣት ሲያርድ፣መንገድም ሲያስፈራ፣የለውዝ ዛፍ ሲያብብ፣አንበጣም ራሱን ሲጐትት፣ፍላጎት ሲጠፋ፤በዚያም ጊዜ ሰው ወደ ዘላለማዊ ቤቱ ይሄዳል፤አልቃሾችም በአደባባዮች ይዞራሉ።

6. የብር ሰንሰለት ሳይበጠስ፣የወርቅ ሳሕንም ሳይሰበር፣የውሃ መቅጃው በምንጩ አጠገብ ሳይከሰከስ፣ወይም መንኰራኵሩ በውሃ ጒድጓድ ላይ ሳይሰበር፣

7. ዐፈር ወደ መጣበት መሬት ሳይመለስ፣መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ፣ፈጣሪህን አስብ።

8. ሰባኪው “ከንቱ ከንቱሁሉም ነገር ከንቱ ነው!” ይላል።

የነገሩ ፍጻሜ

9. ሰባኪው ጥበበኛ ብቻ አልነበረም፤ ነገር ግን ለሕዝቡ ዕውቀትንም ያስተምር ነበር። እርሱም በጥልቅ አሰበ፤ ተመራመረም፤ ብዙ ምሳሌዎችንም በሥርዐት አዘጋጀ።

10. ሰባኪው ትክክለኛውን ቃል ለማግኘት ተመራመረ፤ የጻፈውም ቅንና እውነት ነበረ።

11. የጠቢባን ቃላት እንደ ሹል የከብት መንጃ ናቸው፤ የተሰበሰቡ አባባሎቹም እጅግ ተቀብቅበው እንደ ገቡ ችንካሮች ሲሆኑ፣ ከአንድ እረኛ የተሰጡ ናቸው።

12. ልጄ ሆይ፤ ከዚህ ሁሉ በላይ በማንኛውም ነገር ተጠንቀቅ፤ አንዳችም አትጨምር።ብዙ መጻሕፍትን መጻፍ ማብቂያ የለውም፤ ብዙ ማጥናትም ሰውነትን ያደክማል።

13. እነሆ፤ ሁሉ ነገር ከተሰማ ዘንድ፣የነገሩ ሁሉ ድምዳሜ ይህ ነው፤እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።

14. መልካምም ይሁን ክፉ፣ስውር የሆነውን ነገር ሁሉ አንድ ሳይቀር፣ማንኛውንም ሥራ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።