ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 9:40-55 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

40. ሆኖም አቤሜሌክ አሳደደው፤ እስከ መግቢያው በር ድረስ ባለው መንገድ ሲሸሹም ብዙ ሰዎች ቈስለው ወደቁ።

41. አቤሜሌክ በአሩማ ተቀመጠ፤ ዜቡልም ገዓልንና ወንድሞቹን ከሴኬም አስወጣቸው።

42. በማግስቱ የሴኬም ሕዝብ ወደ ዕርሻ ወጡ፤ ይህም ለአቤሜሌክ ተነገረው፤

43. እርሱም ሰዎቹን አስከትሎ ወጣ፤ ከዚያም ሰዎቹን ሦስት ቦታ መድቦ በዕርሻዎቹ ውስጥ አድፍጠው እንዲጠባበቁ አደረገ። አቤሜሌክ የሴኬም ሰዎች ከከተማዪቱ መውጣታቸውን እንዳየም ካደፈጠበት ሊወጋቸው ተነሣ።

44. ከዚያም አቤሜሌክና አብረውት የነበሩ ምድቦች ቦታ ለመያዝ በፍጥነት ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በሚሮጡበት ጊዜ፣ ሌሎቹ ሁለት ምድቦች ደግሞ እየሮጡ ሄደው በዕርሻው ያሉትን ሁሉ ፈጇቸው።

45. በዚያን ዕለት አቤሜሌክ ቀኑን ሙሉ ከተማዪቱን ሲወጋ ውሎ በመጨረሻ ያዛት፤ሕዝቧን ፈጀ፤ ከተማዪቱንም አጠፋ፤ በላይዋም ጨው ዘራባት።

46. በሴኬም ግምብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ይህን እንደ ሰሙ፤ በኤልበሪት ቤተ መቅደስ ወዳለው ምሽግ ውስጥ ገቡ።

47. አቤሜሌክም በዚያ መመሸጋቸውን ሲሰማ፣

48. እርሱና ሰዎቹ ሁሉ ወደ ሰልሞን ተራራ ወጡ፤ አቤሜሌክም መጥረቢያ ወስዶ ጥቂት የዛፍ ቅርንጫፍ ቈረጠ፤ በትከሻውም ላይ አደረገ። የተከተሉትንም ሰዎች፣ “ፍጠኑ፤ እኔ ሳደርግ ያያችሁትን አድርጉ” ሲል አዘዛቸው።

49. ሰዎቹም ሁሉ ቅርንጫፎች ቈርጠው አቤሜሌክን ተከተሉት፤ ቅርንጫፎቹንም ምሽጉ ላይ አስደግፈው በመከመር ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉ በእሳት አቃጠሏቸው። ስለዚህ በሴኬም ምሽግ ውስጥ የነበሩት አንድ ሺህ ያህል ወንዶችና ሴቶች ሞቱ።

50. ከዚያም አቤሜሌክ ወደ ቴመስ በመሄድ ከተማዪቱን ከቦ ያዛት።

51. ሆኖም በከተማይቱ ውስጥ ብርቱ ግንብ ስለ ነበር፣ የከተማዪቱ ሕዝብ በሙሉ ወንድ ሴት ሳይባል ወደዚያ ሸሹ፤ ደጁንም በውስጥ ዘግተው ወደ ግንቡ ጣሪያ ወጡ።

52. አቤሜሌክም ተዋግቶ ግንቡን ያዘ፤ ይሁን እንጂ እሳት ለመለኮስ ወደ ግንቡ መግቢያ አጠገብ እንደ ደረሰ፣

53. አንዲት ሴት ከላይ የወፍጮ መጅ በራሱ ላይ ለቀቀችበት፤ ጭንቅላቱንም አፈረሰችው።

54. ወዲያውም ጋሻ ጃግሬውን ጠርቶ፣ “ ‘ሴት ገደለችው’ እንዳይሉ እባክህ ሰይፍህን መዘህ ግደለኝ” አለው። ስለዚህ አገልጋዩ ወጋው፤ እርሱም ሞተ።

55. እስራኤላውያንም አቤሜሌክ መሞቱን ሲያዩ ወደ የቤታቸው ተመለሱ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 9