ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 9:24-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. እግዚአብሔር ይህን ያደረገውም፣ በሰባው የይሩበኣል ልጆች ላይ ስለ ተፈጸመው ግፍና ስለ ፈሰሰው ደማቸው፣ ወንድማቸውን አቤሜሌክና ወንድሞቹን እንዲገድል የረዱትን የሴኬም ሰዎች ለመበቀል ነው።

25. የሴኬም ነዋሪዎችም አቤሜሌክን ሸምቀው የሚጠባ በቁትን ሰዎች መደቡ፤ ሰዎቹም እርሱን በመጠባበቅ ላይ ሳሉ በዚያ የሚያልፈውን ሁሉ ዘረፉ፤ ወሬውም ለአቤሜሌክ ደረሰው።

26. በዚህ ጊዜ የአቤድ ልጅ ገዓል ከወንድሞቹ ጋር ወደ ሴኬም መጣ፤ የሴኬምም ሰዎች ተማመኑበት።

27. ወደ ዕርሻ ወጥተው ወይናቸውን ለቅመው ከጨመቁ በኋላ በአምላካቸው ቤት የደስታ በዓል አደረጉ፤ በዚያም እየበሉና እየጠጡ አቤሜሌክን ሰደቡ።

28. የአቤድ ልጅ ገዓል እንዲህ አለ፤ “እንገዛለት ዘንድ አቤሜሌክ ማን ነው? ሴኬምስ ምንድን ናት? እርሱ የይሩበኣል ልጅ አይደለምን? ዜቡልስ የእርሱ ረዳት ሹም አይደለምን? ለሴኬም አባት ለኤሞር ሰዎች ተገዙ፤ ለምን ለአቤሜሌክ እንገዛለን?

29. ምነው ይህን ሕዝብ የማዘው እኔ በሆንሁ ኖሮ!” አቤሜሌክን አስወግደው ነበር፤ ‘ሰራዊትህን አብዝተህ ውጣ! እለው ነበር።’ ”

30. የከተማዪቱ ገዥ ዜቡል፣ የአቤድ ልጅ ገዓል ያለውን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤

31. ወደ አቤሜልክም መልእክተኞች በምስጢር ልኮ እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ የአቤድ ልጅ ገዓልና ወንድሞቹ ወደ ሴኬም መጥተው ከተማዪቱ እንድትሸፍትብህ አድርገዋል።

32. ስለዚህ በሌሊት ሰዎችህን ይዘህ ወጥተህ ሜዳው ላይ ማድፈጥ አለብህ፤

33. ጠዋት ፀሓይ ስትወጣም ወደ ከተማዪቱ ገሥግሥ፤ ገዓልና ሰዎቹ ሊገጥሙህ በሚወጡበት ጊዜ እጅህ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አድርግ።

34. ስለዚህ አቤሜሌክና ሰዎቹ በሙሉ በሌሊት ወጡ፤ በአራት ምድብ ሆነውም በሴኬም አጠገብ አደፈጡ።

35. የአቤድ ልጅ ገዓል ከከተማዪቱ ወጥቶ በመግቢያው በር ላይ ሲቆም፣ አቤሜሌክና ሰዎቹ ካደፈጡበት ወጡ።

36. ገዓል ባያቸው ጊዜ ዜቡልን፣ “ተመልከት፤ ከተራራው ጫፍ ሕዝብ እየወረደ ነው” አለው።ዜቡልም መልሶ፣ “የተራሮች ጥላ ሰዎች መስሎ ተሳስተህ” ነው አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 9