ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 9:19-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. እንግዲህ ዛሬ በይሩበኣልና በቤተ ሰቡ ላይ ያደረጋችሁት በእውነትና በቅንነት ከሆነ እናንተ በአቤሜሌክ ደስ ይበላችሁ፤ እርሱም በእናንተ ደስ ይበለው!

20. ይህ ካልሆነ ግን እሳት ከአቤሜሌክ ትውጣና እናንተን፣ የሴኬምንና የቤት ሚሎን ነዋሪዎች ትብላ፤ እንዲሁም እሳት ከእናንተ፣ ከሴኬምና ከቤትሚሎን ነዋሪዎች ትውጣና አቤሜሌክን ትብላ።”

21. ከዚህ በኋላ ኢዮአታም ሸሽቶ አመለጠ፤ ብኤር ወደተባለች ቦታም መጣ፤ ወንድሙንም አቤሜሌክን ፈርቶ ስለ ነበር እዚያው ይኖር ጀመር።

22. አቤሜሌክ እስራኤልን ሦስት ዓመት ከገዛ በኋላ፣

23. እግዚአብሔር በአቤሜሌክና በሴኬም ነዋሪዎች መካከል ክፉ መንፈስ ሰደደ፤ ስለዚህም የሴኬም ሰዎች አቤሜሌክን ከዱት።

24. እግዚአብሔር ይህን ያደረገውም፣ በሰባው የይሩበኣል ልጆች ላይ ስለ ተፈጸመው ግፍና ስለ ፈሰሰው ደማቸው፣ ወንድማቸውን አቤሜሌክና ወንድሞቹን እንዲገድል የረዱትን የሴኬም ሰዎች ለመበቀል ነው።

25. የሴኬም ነዋሪዎችም አቤሜሌክን ሸምቀው የሚጠባ በቁትን ሰዎች መደቡ፤ ሰዎቹም እርሱን በመጠባበቅ ላይ ሳሉ በዚያ የሚያልፈውን ሁሉ ዘረፉ፤ ወሬውም ለአቤሜሌክ ደረሰው።

26. በዚህ ጊዜ የአቤድ ልጅ ገዓል ከወንድሞቹ ጋር ወደ ሴኬም መጣ፤ የሴኬምም ሰዎች ተማመኑበት።

27. ወደ ዕርሻ ወጥተው ወይናቸውን ለቅመው ከጨመቁ በኋላ በአምላካቸው ቤት የደስታ በዓል አደረጉ፤ በዚያም እየበሉና እየጠጡ አቤሜሌክን ሰደቡ።

28. የአቤድ ልጅ ገዓል እንዲህ አለ፤ “እንገዛለት ዘንድ አቤሜሌክ ማን ነው? ሴኬምስ ምንድን ናት? እርሱ የይሩበኣል ልጅ አይደለምን? ዜቡልስ የእርሱ ረዳት ሹም አይደለምን? ለሴኬም አባት ለኤሞር ሰዎች ተገዙ፤ ለምን ለአቤሜሌክ እንገዛለን?

29. ምነው ይህን ሕዝብ የማዘው እኔ በሆንሁ ኖሮ!” አቤሜሌክን አስወግደው ነበር፤ ‘ሰራዊትህን አብዝተህ ውጣ! እለው ነበር።’ ”

30. የከተማዪቱ ገዥ ዜቡል፣ የአቤድ ልጅ ገዓል ያለውን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤

31. ወደ አቤሜልክም መልእክተኞች በምስጢር ልኮ እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ የአቤድ ልጅ ገዓልና ወንድሞቹ ወደ ሴኬም መጥተው ከተማዪቱ እንድትሸፍትብህ አድርገዋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 9