ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 8:3-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. እግዚአብሔር የምድያማውያንን መሪዎች ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣችሁ፤ ታዲያ እናንተ ከፈጸማችሁት ጋር የሚወዳደር ምን ማድረግ እችል ነበር?” ይህን ሲሰሙ ቍጣቸው በረደ።

4. ጌዴዎንና ሦስት መቶዎቹ ሰዎች ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ ምንም እንኳ ድካም ቢሰማቸውም ጠላቶቻቸውን ያሳድዱ ነበር።

5. የሱኮትንም ሰዎች፣ “የምድያምንም ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን በማሳደድ ላይ ስለ ሆንሁ የተከተሉኝም ሰዎች ስለ ደከሙብኝ እባካችሁ የሚበሉትን እንጀራ ስጧቸው” አላቸው።

6. የሱኮት ሹማምት ግን፣ “ለተከተሉህ ሰዎች እንጀራ እንሰጥ ዘንድ ዛብሄልና ስልማና በእጅህ ገብተዋልን?” አሉት።

7. ጌዴዎንም መልሶ፣ “ደህና፤ እግዚብሔር ዛብሄልንና ስልማናን በእጄ አሳልፎ በሚሰጥበት ጊዜ በምድረ በዳ እሾኽና አሜከላ ሥጋችሁን እተለትላለሁ” አላቸው።

8. ከዚያም ወደ ጵኒኤል ሰዎች ሄዶ ያንኑ ጥያቄ አቀረበላቸው፤ የእነርሱም መልስ የሱኮት ሰዎች ከሰጡት መልስ ጋር አንድ ዐይነት ነበር።

9. እርሱም የጵኒኤልን ሰዎች፣ “በድል አድራጊነት በሰላም ስመለስ ከተማችሁን የምትጠብቁበትን ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ” አላቸው።

10. በዚህ ጊዜ ዛብሄልና ስልማና ዐሥራ አምስት ሺህ ከሆነ ሰራዊታቸው ጋር ቀርቀር በተባለ ስፍራ ነበሩ፤ ይህም ከምሥራቅ ሕዝቦች ከተውጣጣውና በጦር ሜዳ ከወደቀው መቶ ሃያ ሺህ ሰይፍ ታጣቂ ሰራዊት የተረፈው ነበር።

11. ከዚያም ጌዴዎን ተነሣ፤ ከኖባህና ከዮግብሃ በስተ ምሥራቅ የሚኖሩ ዘላኖች የሚሄዱበትን መንገድ ተከትሎ በጠላት ሰራዊት ላይ በድንገት አደጋ ጣለ።

12. ሁለቱ የምድያም ነገሥታት ዛብሄልና ስልማና ሸሹ፤ ጌዴዎን ግን አሳዶ ያዛቸው፤ መላ ሰራዊታቸውንም እጅግ በታተነው።

13. ከዚህ በኋላ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን በሐሬስ መተላለፊያ በኩል አድርጎ ከጦርነቱ ተመለሰ፤

14. እርሱም የሱኮት ሰው የሆነ አንድ ወጣት ማረከ፤ መረመረውም፤ ወጣቱም የሰባ ሰባት የሱኮት ሹማምትና የከተማዪቱንም አለቆች ስም ጻፈለት።

15. ከዚያም ጌዴዎን ወደ ሱኮት ሰዎች መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ ‘ለደከሙት ሰዎችህ እንጀራ እንሰጥ ዘንድ ዛብሄልና ስልማና በእጅህ ገብተዋልን’ በማለት ያላገጣችሁብኝ ዛብሄልና ስልማና እነዚሁላችሁ።”

16. ጌዴዎን የከተማዪቱን አለቆች ወሰደ፤ በምድረ በዳ እሾኽና አሜኬላ በመቅጣት የሱኮትን ሰዎች ትምህርት ሰጣቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 8