ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 8:20-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. ከዚያም ወደ በኵር ልጁ ወደ ዮቴር ዘወር ብሎ፣ “ግደላቸው” አለው፤ ዮቴር ግን ትንሽ ልጅ ነበርና ስለ ፈራ ሰይፉን አልመዘዘም።

21. ዛብሄልና ስልማናም፣ “የሰው ጒልበቱ እንደ ሰውነቱ መጠን ነውና አንተው ራስህ ግደለን አሉት፤ ጌዴዎንም ተነሥቶ ገደላቸው፤ በግመሎቻቸው አንገት ላይ የነበሩትንም ጌጦች ወሰደ።

22. እስራኤላውያንም ጌዴዎንን፣ “ከምድያማውያን እጅ ታድገኸናልና አንተ፣ ልጅህና የልጅ ልጅህ ግዙን” አሉት።

23. ጌዴዎን ግን መልሶ፣ “እኔም ሆንሁ ልጄ አንገዛችሁም፤ የሚገዛችሁ እግዚአብሔር ነው” አላቸው።

24. እርሱም፣ “አንድ የምጠይቃችሁ ነገር አለኝ፤ ይኸውም እያንዳንዳችሁ ከምርኮ ካገኛችሁት ውስጥ የጆሮ ጒትቻችሁን እንድ ትሰጡኝ ነው” አላቸው፤ የወርቅ ጒትቻ ማድረግ የእስማኤላውያን ባህል ነበርና።

25. እነርሱም መልሰው፤ “ደስ እያለን እንሰጥሃለን” አሉት፤ ወዲያው ልብስ አነጠፉ፤ በላዩም ላይ እያንዳንዳቸው ከማረኩት ውስጥ የጆሮ ጒትቻ ጣል ጣል አደረጉለት።

26. ሌሎቹን ጌጣጌጦች ይኸውም የዐንገት ሐብሉን ከነእንጥልጥሉ፣ የምድያም ነገሥታት ይለብሱት የነበረውን ሐምራዊ ልብስ ወይም በግመሎቻቸው ዐንገት ላይ ያሉትን ጌጦች ሳይጨምር ጌዴዎን በጠየቃቸው መሠረት የሰጡት የወርቅ ጒትቻ ክብደት ሺህ ሰባት መቶ ሰቅል ያህል መዘነ።

27. ጌዴዎን በወርቁ ኤፉድ ሠራ፤ በተወለደበትም ከተማ በዖፍራ አኖረው። እስራኤልም በሙሉ ኤፉዱን በማምለክ ስላመነዘሩ፣ ኤፉዱ ለጌዴዎንና ለቤተ ሰቡ ወጥመድ ሆነ።

28. ስለዚህ ምድያማውያን በእስራኤላውያን ተሸነፉ፤ ዳግመኛም ራሳቸውን ከፍ ከፍ አላደረጉም። ጌዴዎን በሕይወት እስካለ ጊዜ ድረስ ምድሪቱ አርባ ዓመት ሰላም አገኘች።

29. የኢዮአስ ልጅ ይሩባኣል ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ በዚያም ተቀመጠ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 8