ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 8:17-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. እንዲሁም በጵኒኤል ያለውን የከተማ መጠበቂያ ግንብ አፈረሰ፤ የከተማዪቱንም ሰዎች ገደለ።

18. ዛብሄልና ስልማናንም፣ “በታቦር ላይ የገደላችኋቸው ሰዎች እንዴት ያሉ ነበሩ?” በማለት ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “ሁሉም እንዲህ እንዳንተ ያሉ የንጉሥ ልጆች የሚመስሉ ናቸው” አሉት።

19. ጌዴዎንም፣ “እነርሱ የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ናቸው፤ ባትገድሏቸው ኖሮ እኔም እንደማልገድላችሁ በሕያው እግዚአብሔር ስም አረጋግጥላችሁ ነበር።” ብሎ መለሰላቸው።

20. ከዚያም ወደ በኵር ልጁ ወደ ዮቴር ዘወር ብሎ፣ “ግደላቸው” አለው፤ ዮቴር ግን ትንሽ ልጅ ነበርና ስለ ፈራ ሰይፉን አልመዘዘም።

21. ዛብሄልና ስልማናም፣ “የሰው ጒልበቱ እንደ ሰውነቱ መጠን ነውና አንተው ራስህ ግደለን አሉት፤ ጌዴዎንም ተነሥቶ ገደላቸው፤ በግመሎቻቸው አንገት ላይ የነበሩትንም ጌጦች ወሰደ።

22. እስራኤላውያንም ጌዴዎንን፣ “ከምድያማውያን እጅ ታድገኸናልና አንተ፣ ልጅህና የልጅ ልጅህ ግዙን” አሉት።

23. ጌዴዎን ግን መልሶ፣ “እኔም ሆንሁ ልጄ አንገዛችሁም፤ የሚገዛችሁ እግዚአብሔር ነው” አላቸው።

24. እርሱም፣ “አንድ የምጠይቃችሁ ነገር አለኝ፤ ይኸውም እያንዳንዳችሁ ከምርኮ ካገኛችሁት ውስጥ የጆሮ ጒትቻችሁን እንድ ትሰጡኝ ነው” አላቸው፤ የወርቅ ጒትቻ ማድረግ የእስማኤላውያን ባህል ነበርና።

25. እነርሱም መልሰው፤ “ደስ እያለን እንሰጥሃለን” አሉት፤ ወዲያው ልብስ አነጠፉ፤ በላዩም ላይ እያንዳንዳቸው ከማረኩት ውስጥ የጆሮ ጒትቻ ጣል ጣል አደረጉለት።

26. ሌሎቹን ጌጣጌጦች ይኸውም የዐንገት ሐብሉን ከነእንጥልጥሉ፣ የምድያም ነገሥታት ይለብሱት የነበረውን ሐምራዊ ልብስ ወይም በግመሎቻቸው ዐንገት ላይ ያሉትን ጌጦች ሳይጨምር ጌዴዎን በጠየቃቸው መሠረት የሰጡት የወርቅ ጒትቻ ክብደት ሺህ ሰባት መቶ ሰቅል ያህል መዘነ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 8