ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 6:31-40 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

31. በዚህ ጊዜ ኢዮአስ በቍጣ ለገነፈለውና በዙሪያው ለነበረው ሕዝብ እንዲህ አለ፤ “ለበኣል ትሟገቱለታላችሁን? ልታድኑትስ ትሞክራላችሁን? ለእርሱ የሚሟገትለት ቢኖር እስከ ጠዋት ይሙት! እንግዲህ በኣል በእርግጥ አምላክ ከሆነ መሠዊያውን ሲያፈርሱበት ራሱን ሊከላከል ይችላል።”

32. ስለዚህም፣ “መሠዊያውን አፍርሶበታልና ራሱ በኣል ይሟገተው” ሲሉ በዚያ ዕለት ጌዴዎንን፣ “ይሩበኣል” ብለው ጠሩት።

33. በዚህ ጊዜ ምድያማውያን ሁሉ፣ አማሌቃውያንና ሌሎች የምሥራቅ ሕዝቦች ኀይላቸውን አስተባብረው የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር በኢይዝራኤል ሸለቆ ሰፈሩ።

34. ከዚያም የእግዚአብሔር መንፈስ በጌዴዎን ላይ ወረደ፤ እርሱም መለከት ነፋ፤ አቢዔዝራውያን እንዲከተሉት ጠራቸው።

35. እንዲሁም በመላው የምናሴ ምድር መልእክተኞቹን ልኮ እንዲከተሉት ጥሪ አደረገ፤ ደግሞም የአሴር፣ የዛብሎንና የንፍታሌም ሰዎች ወጥተው እንዲገጥሟቸው መልእክተኛ ላከባቸው።

36. ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “በተናገርኸው መሠረት እስራኤላውያንን በእጄ የምታድናቸው ከሆነ፣

37. እነሆ፤ የበግ ጠጒር ባዘቶ በዐውድማው ላይ አኖራለሁ። ምድሩ በሙሉ ደረቅ ሆኖ ባዝቶው ላይ ብቻ ጤዛ ቢኖር፣ እንዳልኸው እስራኤላውያንን በእኔ እጅ እንደምታድናቸው ዐውቃለሁ።”

38. እንደዚሁ ሆነ፤ ጌዴዎን በማግስቱ ጠዋት ማልዶ ተነሣ፤ ባዘቶውንም ሲጨምቅ የወጣው ውሃ አንድ ቈሬ ሞላ።

39. ከዚያም ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “እባክህ አትቈጣኝ፤ አንዲት ጥያቄ እንደ ገና ልጠይቅ። በጠጒሩ ባዘቶ ላይ ሌላ ሙከራ እንዳደርግ ፍቀድልኝ፤ በዚህ ጊዜ ምድሩ ሁሉ በጤዛ ተሸፍኖ ባዘቶው ደረቅ ይሁን።”

40. በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር እንደ ተጠየቀው አደረገ፤ ምድሩ በሙሉ በጤዛ ሲሸፈን፣ ባዘቶው ብቻ ደረቅ ሆነ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 6