ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 6:2-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. እስራኤላውያን የምድያማውያን ኀይል ስለ በረታባቸው በየዋሻውና በየምሽጉ፣ በየተራራው ጥግ መሸሸጊያ ስፍራ አበጁ።

3. እስራኤላውያን ዘር በሚዘሩበት ጊዜ ሁሉ ምድያማውያን፣ አማሌቃውያንና ሌሎች የምሥራቅ ሕዝቦች መጥተው አገሩን ይወሩ ነበር።

4. እነርሱም በምድሪቱ ላይ ሰፍረው እስከ ጋዛ ያለውን ሰብል በማጥፋት አንዳችም የእህል ዘር አያስተርፉም፣ የበግም ሆነ የከብት ወይም የአህያ መንጋ አይተዉም ነበር።

5. ከብቶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው ሲመጡ ልክ የአንበጣ መንጋ ይመስሉ ነበር፤ ሰዎቹንም ሆነ ግመሎቻቸውን ለመቍጠር አዳጋች ሲሆን፣ የሚመጡትም ምድሪቱን ለማጥፋት ነበር።

6. ምድያማውያን እስራኤላውያንን ችግር ላይ ስለጣሏቸው፣ ይረዳቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።

7. ከምድያማውያን ጥቃት የተነሣ እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤

8. እግዚአብሔር አንድ ነቢይ ላከላቸው፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ነኝ።

9. ከግብፃውያን እጅ ታደግኋችሁ፤ ከሚያስ ጨንቋችሁ ሁሉ አዳንኋችሁ፤ እነርሱንም ከፊታችሁ አሳድጄ አስወጣኋቸው፤ ምድራቸውንም ሰጠኋችሁ።

10. እናንተንም፣ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ በምድራቸው ላይ የምትኖሩባቸው የአሞራውያንን አማልክት አታምልኩ አልኋችሁ፤ እናንተ ግን አላዳመጣችሁኝም።”

11. የእግዚአብሔር መልአክ ዖፍራ ወደምትባል መንደር መጥቶ፣ በአቢዔዝራዊው በኢዮአስ ዕርሻ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የባሉጥ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን፣ ምድያማውያን እንዳያዩበት ደብቆ በወይን መጭመቂያው ስፍራ ስንዴውን ይወቃ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 6