ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 4:16-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. ባርቅ ግን የሲሣራን ሠረገሎችና ሰራዊቱን እስከ አሪሶት ሐጎይም ድረስ አሳደዳቸው፤ የሲሣራ ሰራዊት በሙሉ በሰይፍ ወደቀ፤ በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው አልነበረም።

17. በሐጾር ንጉሥ በኢያቡስና በቄናዊው በሔቤር ጐሣ መካከል መልካም ግንኙነት ስለ ነበር ሲሣራ በእግሩ ሸሽቶ የቄናዊው የሔቤር ሚስት ወደሆነችው ወደ ኢያዔል ድንኳን ሮጠ።

18. ኢያዔልም ወጥታ ሲሣራን ተቀበለችውና፣ “ጌታዬ፤ ወደ ውስጥ ግባ፤ ፈጽሞ አትፍራ” አለችው፤ ሲሣራም ወደ ድንኳኗ ገባ፤ እርሷም በልብስ ሸፍና ደበቀችው።

19. ሲሣራም፣ “ጠምቶኛልና እባክሽን ውሃ አጠጪኝ” አላት፤ እርሷም የወተት ጮጮውን ከፍታ የሚጠጣውን ሰጠችው፤ እንደ ገናም ሸፈነችው።

20. እርሱም፣ “በድንኳኑ በር ላይ ቁሚ፤ ማንም ሰው መጥቶ፣ “እዚህ ሰው አለ?” ቢልሽ፣ “የለም በይ” አላት።

21. የሔቤር ሚስት ኢያዔል ግን ሲሣራ ደክሞ፣ ከባድ እንቅልፍም ወስዶት ሳለ፣ የድንኳን ካስማና መዶሻ ይዛ በቀስታ ወደ እርሱ ቀረበች፤ ከዚያም ካስማውን በመዶሻ ጆሮ ግንዱ ላይ መትታ ከመሬት ጋር ሰፋችው፤ እርሱም ሞተ።

22. ባርቅ ሲሣራን በመከታተል ላይ ስለ ነበር ከዚያ ሲደርስ፣ ኢያዔል ከድንኳኗ ወጥታ “ና፤ የምትፈልገውን ሰው አሳይሃለሁ” አለችው፤ ስለዚህ ከእርሷ ጋር ወደ ድንኳንዋ ገባ፤ ሲሣራም በጆሮ ግንዱ ላይ ካስማ እንደ ተመታበት ሞቶ ተዘርሮ ነበረ።

23. በዚያች ዕለት እግዚአብሔር የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስን በእስራኤላውያን ፊት እንዲሸነፍ አደረገው፤

24. ከነዓናዊውን ንጉሥ ኢያቢስን እስኪደመስሱ ድረስ የእስራኤላውያን ክንድ እየበረታ ሄደ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 4