ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 3:25-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. እስኪደክማቸውም ድረስ ጠበቁ፤ ነገር ግን ንጉሡ የእልፍኙን በሮች ባለመክፈቱ ቍልፍ ወስደው ከፈቱ፤ በዚያም ጌታቸው ሞቶ፣ በወለሉም ላይ ተዘርግቶ አገኙት።

26. የንጉሡ አገልጋዮች በዕልፍኙ በር ላይ ቆመው ሲጠባበቁ ናዖድ ርቆ ሄደ፤ ድንጋዮች ተጠርበው በሚወጡበት በኩል ወደ ሴርታይም አመለጠ።

27. እዚያም እንደ ደረሰ፣ በኰረብታማው በኤፍሬም ምድር ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ እስራኤላውያንም በእርሱ መሪነት ከኰረብታው ላይ አብረውት ወረዱ።

28. እርሱም፣ “ጠላታችሁን ሞዓብን እግዚአብሔር በእጃችሁ አሳልፎ ስለ ሰጣችሁ ተከተሉኝ” በማለት አዘዛቸው፤ እነርሱም ተከትለውት ወረዱ፤ ከዚያም ከዮርዳኖስ ወደ ሞዓብ የሚያሻግሩትን መልካዎች በመያዝ አንድም ሰው እንዳያልፍ ከለከሉ።

29. በዚያን ጊዜ ብርቱና ኀይለኛ የሆኑ ዐሥር ሺህ ሞዓባውያንን ገደሉ፤ አንድም ሰው አላመለጠም።

30. በዚያን ቀን ሞዓብ በእስራኤል ድል ሆነች፤ ምድሪቱም ለሰማንያ ዓመት ሰላም አገኘች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 3