ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 20:14-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ስለዚህ እስራኤላውያንን ለመውጋት ከየከተሞቻቸው በአንድነት ወደ ጊብዓ መጡ።

15. ብንያማውያንም ከመላው የጊብዓ ነዋሪዎች መካከል ከተመረጡት ሰባት መቶ ሰዎች ሌላ፣ ሰይፍ የታጠቁ ሃያ ስድስት ሺህ ሰዎች በአንድ አፍታ ከየከተሞቻቸው በተጨማሪ አሰባሰቡ።

16. በእነዚህም ሁሉ መካከል እያንዳንዳቸው ድንጋይ ወንጭፈው ጠጒር እንኳ የማይስቱ ሰባት መቶ ምርጥ ግራኞች ነበሩ።

17. እስራኤላውያን፣ ብንያማውያንን ሳይጨምር፣ ሰይፍ የታጠቁ አራት መቶ ሺህ ተዋጊዊች አሰባሰቡ።

18. እስራኤላውያን ወደ ቤቴል ወጡ፤ እግዚአብሔርንም፣ “ብንያማውያንን ለመውጋት ከመካከላችን ማን ቀድሞ ይውጣ?” ሲሉ ጠየቁ። እግዚአብሔርም፣ “ይሁዳ ቀድሞ ይውጣ” ብሎ መለሰ።

19. በማግሥቱ ጧት እስራኤላውያን ተነሥተው በጊብዓ አጠገብ ሰፈሩ፤

20. የእስራኤል ሰዎች ብንያማውያንን ለመውጋት ሄዱ፤ በጊብዓ ለሚያደርጉትም ውጊያ ቦታ ቦታቸውን ያዙ።

21. ብንያማውያን ከጊብዓ ወጡ፤ በዚያችም ዕለት ከእስራኤላውያን ሃያ ሁለት ሺህ ሰዎች ገደሉ።

22. ይሁን እንጂ እስራኤላውያን እርስ በርሳቸው ተበረታትተው በመጀመሪያው ቀን ተሰልፈው በነበረበት ስፍራ ላይ እንደ ገና ቦታ ቦታቸውን ያዙ።

23. እስራኤላውያን ወጥተው እስኪመሽ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት አለቀሱ፤ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን ለመግጠም እንደ ገና እንውጣን?” ብለው እግዚአብሔርን ጠየቁ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን፤ ውጡና ግጠሟቸው” ብሎ መለሰላቸው።

24. በሁለተኛው ቀን እስራኤላውያን ወደ ብንያማውያን ተጠጉ።

25. በዚሁ ጊዜም ብንያማውያን፣ እስራኤላውያንን ሊወጉ ከጊብዓ ወጡ፤ እንደ ገናም በሙሉ ሰይፍ የታጠቁ ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች ገደሉ።

26. የእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ ወደ ቤቴል ወጡ፤ እዚያም እያለቀሱ በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፤ በዚያን ቀን እስኪመሽ ድረስ ጾሙ፤ በእግዚአብሔር ፊት የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ።

27. እስራኤላውያንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠየቁ፤ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት እዚያው ነበር፤

28. የአሮን ልጅ፤ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስም በፊቱ ይቆም ነበር። እስራኤላውያንም፣ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን እንደ ገና ሄደን ጦርነት እንግጠማቸው ወይስ ይቅር?” ሲሉ ጠየቁ። እግዚአብሔርም፣ “ሂዱ፤ በነገው ዕለት በእጃችሁ እሳልፌ እሰጣችኋለሁ” አላቸው።

29. ከዚያም እስራኤላውያን በጊብዓ ዙሪያ ድብቅ ጦር አኖሩ።

30. በሦስተኛውም ቀን ብንያማውያንን ለመውጋት ወጡ፤ ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሁሉ ጊብዓን ለመውጋት ቦታ ቦታቸውን ያዙ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 20