ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 19:5-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. በአራተኛው ቀን ማልደው ተነሡ፤ እንግዳውም ለመሄድ ተዘጋጀ፤ የልጂቱ አባት ግን፣ “እንድትበረታ እህል ቅመስ፤ ከዚያም መሄድ ትችላለህ” አለው።

6. ስለዚህ ሁለቱ ለመብላትና ለመጠጣት አብረው ተቀመጡ። የልጂቷም አባት፣ “እባክህ ዛሬም እዚሁ አድረህ ተደሰት” አለው።

7. ሰውየው ለመሄድ ሲነሣም ዐማቱ እንዲያድር ለመነውና እዚያው አደረ።

8. በአምስተኛውም ቀን ጠዋት ሌዋዊው ለመሄድ ሲነሣ፣ የልጂቱ አባት “ሰውነትህን አበርታ፤ ጥላው እስኪበርድም ድረስ በዚሁ ቈይ” አለው፤ ስለዚህ ሁለቱም አብረው በሉ።

9. ሰውየውም ከቁባቱና ከአገልጋዩ ጋር ለመሄድ በተነሣ ጊዜ፣ የልጅቱ አባት ዐማቱ “እነሆ ጊዜው እየመሸ ነው፤ እዚሁ እደሩ፤ ቀኑ እየተገባደደ ነው፤ እዚሁ አድራችሁ ተደሰቱ፤ ነገ ጠዋት ማልዳችሁ በመነሣት መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ” አለው።

10. ሌዋዊው ግን በዚያች ሌሊት በዚያ ለማደር ስላልፈለገ ተነሥቶ የተጫኑትን ሁለቱን አህዮቹንና ቁባቱን ይዞ ኢየሩሳሌም ወደተባለችው ወደ ኢያቡስ ሄደ።

11. ወደ ኢያቡስ እንደ ቀረቡም ጊዜው እየመሸ ስለ ነበር አገልጋዩ ጌታውን፣ “እንግዲህ ወደዚህች ወደ ኢያቡሳውያን ከተማ ጐራ ብለን እንደር” አለው።

12. ጌታውም፣ “አይሆንም፤ ሕዝቧ እስራኤላዊ ወዳልሆነ ወደ ባዕድ ከተማ አንገባም፤ ወደ ጊብዓ አልፈን እንሂድ” አለው።

13. ቀጥሎም፣ “በል ና፤ ወደ ጊብዓ ወይም ወደ ራማ ለመድረስ እንሞክርና ከዚያ በአንዱ ስፍራ እናድራለን” አለው።

14. ስለዚህም መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ የብንያም ነገድ ወደሆነችው ወደ ጊብዓ እንደ ደረሱም ፀሓይ ጠለቀች።

15. ለማደርም ወደዚያው ጎራ አሉ፤ ሄደውም በከተማዪቱ አደባባይ ተቀመጡ፤ ሆኖም በቤቱ ለማሳደር ማንም አልተቀበላቸውም ነበር።

16. በዚያች ምሽት ከኰረብታማው ከኤፍሬም አገር መጥቶ በጊብዓ የሚኖር አንድ መጻተኛ ሽማግሌ ከዕርሻ ሥራው መጣ፤ የዚያ አገር ሰዎች ግን ብንያማውያን ነበሩ።

17. ሽማግሌው ቀና ብሎ መንገደኛውን በከተማዪቱ አደባባይ ላይ ባየው ጊዜ፣ “ከወዴት መጣህ? ወዴትስ ትሄዳለህ?” ሲል ጠየቀው።

18. ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኛ የመጣነው ከይሁዳ ቤተ ልሔም ርቆ ከሚገኘው ከኰረብታማው ከኤፍሬም አገር ነው፤ ከይሁዳ ቤተ ልሔም ነበርሁ፤ አሁን ወደ እግዚአብሔር ቤት እሄዳለሁ፤ ወደ ቤቱ የሚወስደኝ ሰው አላገኘሁም።

19. ለአህዮቻችን ገለባና ገፈራ አለን፤ እኛ ባሮችህ ለእኔም ሆነ ለገረድህ፣ አብሮን ላለውም ወጣት እንጀራና የወይን ጠጅ ይዘናል፤ ሌላ ምንም ነገር አያስፈልገንም።”

20. ሽማግሌውም፣ “ኑ ግቡ በቤቴም እደሩ፤ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አቀርባለሁ፤ በአደባባይ ግን አትደሩ” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 19