ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 19:17-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ሽማግሌው ቀና ብሎ መንገደኛውን በከተማዪቱ አደባባይ ላይ ባየው ጊዜ፣ “ከወዴት መጣህ? ወዴትስ ትሄዳለህ?” ሲል ጠየቀው።

18. ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኛ የመጣነው ከይሁዳ ቤተ ልሔም ርቆ ከሚገኘው ከኰረብታማው ከኤፍሬም አገር ነው፤ ከይሁዳ ቤተ ልሔም ነበርሁ፤ አሁን ወደ እግዚአብሔር ቤት እሄዳለሁ፤ ወደ ቤቱ የሚወስደኝ ሰው አላገኘሁም።

19. ለአህዮቻችን ገለባና ገፈራ አለን፤ እኛ ባሮችህ ለእኔም ሆነ ለገረድህ፣ አብሮን ላለውም ወጣት እንጀራና የወይን ጠጅ ይዘናል፤ ሌላ ምንም ነገር አያስፈልገንም።”

20. ሽማግሌውም፣ “ኑ ግቡ በቤቴም እደሩ፤ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አቀርባለሁ፤ በአደባባይ ግን አትደሩ” አለው።

21. ስለዚህ ወደ ቤቱ አስገብቶት ለአህዮቹ ገፈራ ሰጣቸው፤ እንግዶቹም እግራቸውን ታጠቡ፤ በሉ፤ ጠጡም።

22. በግብዣው ላይ እየተደሰቱ ሳለ፣ ጥቂት የከተማዪቱ ወስላቶች ቤቱን ከበቡ፤ በሩንም እየደበደቡ፣ “ዝሙት እንድንፈጽምበት ቤትህ የገባውን ሰው አውጣው” በማለት የቤቱ ባለቤት በሆነው ሽማግሌ ላይ ጮኹበት።

23. የቤቱም ባለቤት ወደ ውጭ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “የለም ወዳጆቼ፤ እንዲህ አትሁኑ፤ ሰውየው እንግዳዬ ስለ ሆነ ይህን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙ።

24. እነሆ ድንግል የሆነች ልጄና የሰውየው ቊባት አሉ፤ እነርሱን አሁኑኑ ላውጣላችሁና አስነውሯቸው፤ ያሻችሁንም አድርጉባቸው፤ በዚህ ሰው ላይ ግን እንዲህ ያለውን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙበት።”

25. ሆኖም ሰዎቹ ሊሰሙት አልፈለጉም፤ ስለዚህ ሌዋዊው ቁባቱን ወደ ውጭ አወጣላቸው፤ ሰዎቹም አመነዘሩባት፤ ሌሊቱን ሙሉ ሲፈራረቁባት አድረው ጐሕ ሲቀድ ለቀቋት።

26. በነጋም ጊዜ ሴቲቱ ጌታዋ ወዳለበት ቤት ተመልሳ ሄደች። ደጃፉ ላይ ወድቃ ፀሓይ እስክትወጣ ድረስ እዚያው ተዘረረች።

27. ጌታዋ በጠዋት ተነሥቶ በሩን በመክፈት መንገዱን ለመቀጠል ሲወጣ፣ ቁባቱ እጅዋን ከደጃፉ መድረክ ላይ እንደ ዘረጋች ከቤቱ በራፍ ላይ ተዘርራ ወድቃ አገኛት።

28. ሌዋዊውም፣ “በዪ ተነሺና እንሂድ” አላት፤ ነገር ግን መልስ አልነበረም። ከዚያም በአህያው ላይ ከጫናት በኋላ ወደ ቤቱ ጒዞውን ቀጠለ።

29. ቤቱ እንደ ደረሰም ቢላዋ አንሥቶ ቁባቱን ዐሥራ ሁለት ቦታ በመቈራረጥ ወደ እስራኤል ምድር ሁሉ ሰደደ።

30. ያየም ሁሉ፣ “እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ጀምሮ እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አልታየም፤ አልተደረገም፤ ምን ማድረግ እንዳለብንም በነገሩ አስቡበት፤ ተመካከሩበት” ተባባሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 19