ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 19:10-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ሌዋዊው ግን በዚያች ሌሊት በዚያ ለማደር ስላልፈለገ ተነሥቶ የተጫኑትን ሁለቱን አህዮቹንና ቁባቱን ይዞ ኢየሩሳሌም ወደተባለችው ወደ ኢያቡስ ሄደ።

11. ወደ ኢያቡስ እንደ ቀረቡም ጊዜው እየመሸ ስለ ነበር አገልጋዩ ጌታውን፣ “እንግዲህ ወደዚህች ወደ ኢያቡሳውያን ከተማ ጐራ ብለን እንደር” አለው።

12. ጌታውም፣ “አይሆንም፤ ሕዝቧ እስራኤላዊ ወዳልሆነ ወደ ባዕድ ከተማ አንገባም፤ ወደ ጊብዓ አልፈን እንሂድ” አለው።

13. ቀጥሎም፣ “በል ና፤ ወደ ጊብዓ ወይም ወደ ራማ ለመድረስ እንሞክርና ከዚያ በአንዱ ስፍራ እናድራለን” አለው።

14. ስለዚህም መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ የብንያም ነገድ ወደሆነችው ወደ ጊብዓ እንደ ደረሱም ፀሓይ ጠለቀች።

15. ለማደርም ወደዚያው ጎራ አሉ፤ ሄደውም በከተማዪቱ አደባባይ ተቀመጡ፤ ሆኖም በቤቱ ለማሳደር ማንም አልተቀበላቸውም ነበር።

16. በዚያች ምሽት ከኰረብታማው ከኤፍሬም አገር መጥቶ በጊብዓ የሚኖር አንድ መጻተኛ ሽማግሌ ከዕርሻ ሥራው መጣ፤ የዚያ አገር ሰዎች ግን ብንያማውያን ነበሩ።

17. ሽማግሌው ቀና ብሎ መንገደኛውን በከተማዪቱ አደባባይ ላይ ባየው ጊዜ፣ “ከወዴት መጣህ? ወዴትስ ትሄዳለህ?” ሲል ጠየቀው።

18. ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኛ የመጣነው ከይሁዳ ቤተ ልሔም ርቆ ከሚገኘው ከኰረብታማው ከኤፍሬም አገር ነው፤ ከይሁዳ ቤተ ልሔም ነበርሁ፤ አሁን ወደ እግዚአብሔር ቤት እሄዳለሁ፤ ወደ ቤቱ የሚወስደኝ ሰው አላገኘሁም።

19. ለአህዮቻችን ገለባና ገፈራ አለን፤ እኛ ባሮችህ ለእኔም ሆነ ለገረድህ፣ አብሮን ላለውም ወጣት እንጀራና የወይን ጠጅ ይዘናል፤ ሌላ ምንም ነገር አያስፈልገንም።”

20. ሽማግሌውም፣ “ኑ ግቡ በቤቴም እደሩ፤ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አቀርባለሁ፤ በአደባባይ ግን አትደሩ” አለው።

21. ስለዚህ ወደ ቤቱ አስገብቶት ለአህዮቹ ገፈራ ሰጣቸው፤ እንግዶቹም እግራቸውን ታጠቡ፤ በሉ፤ ጠጡም።

22. በግብዣው ላይ እየተደሰቱ ሳለ፣ ጥቂት የከተማዪቱ ወስላቶች ቤቱን ከበቡ፤ በሩንም እየደበደቡ፣ “ዝሙት እንድንፈጽምበት ቤትህ የገባውን ሰው አውጣው” በማለት የቤቱ ባለቤት በሆነው ሽማግሌ ላይ ጮኹበት።

23. የቤቱም ባለቤት ወደ ውጭ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “የለም ወዳጆቼ፤ እንዲህ አትሁኑ፤ ሰውየው እንግዳዬ ስለ ሆነ ይህን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 19