ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 15:8-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ክፉኛ መታቸው፤ ከነርሱም ብዙዎችን ገደለ፤ ከዚያም ወርዶ በኢታም ዐለት ዋሻ ተቀመጠ።

9. ፍልስጥኤማውያን ወጥተው በይሁዳ ሰፈሩ፤ ከዚያም በሌሒ አጠገብ ተበታትነው አደፈጡ።

10. የይሁዳም ሰዎች፣ “ልትወጉን የመጣችሁት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው።እነርሱም “እኛ የመጣነው ሳምሶንንልና ስርና ያደረገብንን ልናደርግበት ነው” ብለው መለሱላቸው።

11. ከዚያም ሦስት ሺህ ሰዎች ከይሁዳ ተነሥተው በኤታም ዐለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሳምሶንን፣ “ፍልስጥኤማውያን ገዦቻችን መሆናቸውን አታውቅምን? ያደረግህብንስ ነገር ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።ሳምሶንም፣ “ያደረግሁት እነርሱ ያደረጉብኝን ነው” በማለት መለሰላቸው።

12. እነርሱም፣ “አስረን ለፍልስጥኤማውያን ልንሰጥህ ይኸው መጥተናል” አሉት።ሳምሶንም፣ “እናንተ ራሳችሁ ላትገድሉኝ ማሉልኝ” አላቸው።

13. እነርሱም፣ “አስረን ብቻ ለእነርሱ አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ ራሳችን አንገድልህም” አሉት፤ ከዚያ በሁለት አዳዲስ ገመድ አስረው ከዐለቱ ዋሻ አወጡት።

14. ሳምሶን ሌሒ እንደ ደረሰም ፍልስጥኤማውያን እየጮኹ ወደ እርሱ መጡ፤ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳምሶን ላይ በኀይል ወረደበት። እጆቹ የታሰሩበትም ገመድ እሳት ውስጥ እንደ ገባ የተልባ እግር ፈትል ሆኖ ከእጆቹ ላይ ወደቀ።

15. ከዚያም በቅርቡ የሞተ የአንድ የአህያ መንጋጋ አይቶ ከመሬት አነሣ፤ በዚያም አንድ ሺህ ሰው ገደለ።

16. ሳምሶንም፣“በአንድ የአህያ መንጋጋ፣ሺህ ሰው ዘራሪ፤በአንድ የአህያ መንጋጋ፣ሺህ ሬሳ አነባባሪ፡ ብሎ ፎከረ።

17. ይህን ተናግሮ እንዳበቃ የአህያውን መንጋጋ ከእጁ ወዲያ ወረወረው፤ የዚያም ቦታ ስም ራማት ሌሒ ተብሎ ተጠራ።

18. እጅግ ተጠምቶ ስለ ነበር፤ “እነሆ፤ ለአገልጋይህ ይህን ታላቅ ድል አጐናጽፈሃል፤ ታዲያ አሁን በውሃ ጥም ልሙት? እንዴትስ በእነዚህ ባልተገረዙ ፍልስጥኤማውያን እጅ ልውደቅ? በማለት ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።

19. እግዚአብሔርም በሌሒ ዐለት ሰነጠቀለት፤ ከዚያም ውኃ ወጣ፤ ሳምሶንም ያን ሲጠጣ በረታ፤ መንፈሱም ታደሰ። ስለዚህ ያ ምንጭ ዓይንሀቆሬ ተባለ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያው በሌሒ ይገኛል።

20. ሳምሶንም በፍልስጥኤማውያን ዘመን በእስራኤል ላይ ለሃያ ዓመት ፈራጅ ሆነ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 15