ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 11:7-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ዮፍታሔም፣ “ምነው ጠልታችሁኝ ከአባቴ ቤት አሳዳችሁኝ አልነበረምን? ታዲያ አሁን ችግር ሲገጥማችሁ ነው የምትፈልጉኝ?” አላቸው።

8. የገለዓድ አለቆችም፣ “እንግዲህ አሁን ወደ አንተ መጥተናል፤ አሞናውያንን እንድንወጋ በል ተነሥና አብረን እንሂድ፤ በገለዓድ በምንኖረው በሁላችንም ላይ አለቃ ትሆናለህ” አሉት።

9. ዮፍታሔም፣ “አሞናውያንን ለመውጋት ወደ አገሬ ብትመልሱኝና እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው በእርግጥ አለቃችሁ እሆናለሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

10. የገለዓድ አለቆችም፣ “እግዚአብሔር ምስክራችን ነው፤ ያልከውንም በእርግጥ እናደርጋለን” አሉት።

11. ስለዚህ ዮፍታሔ ከገለዓድ አለቆች ጋር ሄደ፤ ሕዝቡም በላያቸው ላይ አለቃና አዛዥ አደረጉት፤ ዮፍታሔም የተናገረውን ቃል ሁሉ ምጽጳ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ደገመው።

12. ከዚያም ዮፍታሔ ወደ አሞናውያን ንጉሥ፣ “ከእኔ ጋር ምን ጠብ ቢኖርህ ነው መጥተህ አገሬን የወጋኸው?” በማለት መልእክተኞች ላከ።

13. የአሞናውያንም ንጉሥ ለዮፍታሔ መልእክተኞች፣ “ይህን ያደረግሁት እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ በአርኖንና በያቦቅ ወንዞች መካከል ያለውንና እስከ ዮርዳኖስ ያለውን አገሬን ስለ ወሰዱብኝ ነው፤ አሁንም በሰላም መልሱልኝ” አላቸው።

14. ዮፍታሔም መልእክተኞቹን እንደ ገና ወደ አሞናውያን ንጉሥ ላካቸው፤

15. እንዲህም አላቸው፤ “ዮፍታሔ እንዲህ ይላል፤ እስራኤል የሞዓብንም ሆነ የአሞናውያንን ምድር አልወሰደም።

16. እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ በምድረ በዳ አድርጎ ወደ ቀይ ባሕር ከዚያም ወደ ቃዴስ ሄደ።

17. እስራኤልም ወደ ኤዶም ንጉሥ፣ ‘በአገርህ እንዳልፍ እባክህ ፍቀድልኝ’ በማለት መልእክተኞችን ላከበት፤ የኤዶም ንጉሥ ግን አልሰማውም። ለሞዓብ ንጉሥም እንደዚሁ ላከበት፤ እርሱም አልተቀበለውም፤ ስለዚህ እስራኤል በቃዴስ ተቀመጠ።

18. “ቀጥሎም የኤዶምንና የሞዓብን ምድር በመዞር፣ በምድረ በዳው ተጒዞ ከሞዓብ በስተ ምሥራቅ በኩል በማለፍ ከአርኖን ማዶ ሰፈረ፤ የሞዓብም ድንበር አርኖን ስለ ነበር ወደ ሞዓብ ክልል አልገባም።

19. “ከዚያም እስራኤል በሐሴቦን ወዳለው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልእክተኞች ልኮ፣ ‘ወደ ገዛ ስፍራችን ለመሄድ በአገርህ እንዳልፍ ፍቀድልኝ’ አለው።

20. ሴዎን ግን በግዛቱ እንዲያልፍ ለመፍቀድ እስራኤልን አላመነውም፤ ሰራዊቱንም ሰብስቦ በያሃድ ከሰፈረ በኋላ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 11