ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 11:3-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ስለዚህም ዮፍታሔ ከወንድሞቹ ሸሽቶ መኖሪያውን ጦብ በተባለች ምድር አደረገ፤ እዚያም ወሮበሎች ተሰባስበው ተከተሉት።

4. ከጥቂት ጊዜ በኋላም አሞናውያን በእስራኤል ላይ ጦርነት ባደረጉ ጊዜ፣

5. የገለዓድ አለቆች ዮፍታሔን ለማምጣት ወደ ጦብ ምድር ሄዱ።

6. እነርሱም፣ “ከአሞናውያን ጋር መዋጋት እንችል ዘንድ መጥተህ ምራን” አሉት።

7. ዮፍታሔም፣ “ምነው ጠልታችሁኝ ከአባቴ ቤት አሳዳችሁኝ አልነበረምን? ታዲያ አሁን ችግር ሲገጥማችሁ ነው የምትፈልጉኝ?” አላቸው።

8. የገለዓድ አለቆችም፣ “እንግዲህ አሁን ወደ አንተ መጥተናል፤ አሞናውያንን እንድንወጋ በል ተነሥና አብረን እንሂድ፤ በገለዓድ በምንኖረው በሁላችንም ላይ አለቃ ትሆናለህ” አሉት።

9. ዮፍታሔም፣ “አሞናውያንን ለመውጋት ወደ አገሬ ብትመልሱኝና እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው በእርግጥ አለቃችሁ እሆናለሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

10. የገለዓድ አለቆችም፣ “እግዚአብሔር ምስክራችን ነው፤ ያልከውንም በእርግጥ እናደርጋለን” አሉት።

11. ስለዚህ ዮፍታሔ ከገለዓድ አለቆች ጋር ሄደ፤ ሕዝቡም በላያቸው ላይ አለቃና አዛዥ አደረጉት፤ ዮፍታሔም የተናገረውን ቃል ሁሉ ምጽጳ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ደገመው።

12. ከዚያም ዮፍታሔ ወደ አሞናውያን ንጉሥ፣ “ከእኔ ጋር ምን ጠብ ቢኖርህ ነው መጥተህ አገሬን የወጋኸው?” በማለት መልእክተኞች ላከ።

13. የአሞናውያንም ንጉሥ ለዮፍታሔ መልእክተኞች፣ “ይህን ያደረግሁት እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ በአርኖንና በያቦቅ ወንዞች መካከል ያለውንና እስከ ዮርዳኖስ ያለውን አገሬን ስለ ወሰዱብኝ ነው፤ አሁንም በሰላም መልሱልኝ” አላቸው።

14. ዮፍታሔም መልእክተኞቹን እንደ ገና ወደ አሞናውያን ንጉሥ ላካቸው፤

15. እንዲህም አላቸው፤ “ዮፍታሔ እንዲህ ይላል፤ እስራኤል የሞዓብንም ሆነ የአሞናውያንን ምድር አልወሰደም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 11