ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 11:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ገለዓዳዊው ዮፍታሔ ኀያል ጦረኛ ነበረ፤ አባቱ ገለዓድ ነበር፤ እናቱም ጋለሞታ ነበረች።

2. እንደዚሁም የገለዓድ ሚስት ለገለዓድ ወንዶች ልጆች ወለደችለት፤ እነርሱም ባደጉ ጊዜ ዮፍታሔን፣ “ከሌላ ሴት ስለ ተወለድህ ከቤተ ሰባችን ምንም ዐይነት ውርስ አይገባህም” በማለት አሳደዱት።

3. ስለዚህም ዮፍታሔ ከወንድሞቹ ሸሽቶ መኖሪያውን ጦብ በተባለች ምድር አደረገ፤ እዚያም ወሮበሎች ተሰባስበው ተከተሉት።

4. ከጥቂት ጊዜ በኋላም አሞናውያን በእስራኤል ላይ ጦርነት ባደረጉ ጊዜ፣

5. የገለዓድ አለቆች ዮፍታሔን ለማምጣት ወደ ጦብ ምድር ሄዱ።

6. እነርሱም፣ “ከአሞናውያን ጋር መዋጋት እንችል ዘንድ መጥተህ ምራን” አሉት።

7. ዮፍታሔም፣ “ምነው ጠልታችሁኝ ከአባቴ ቤት አሳዳችሁኝ አልነበረምን? ታዲያ አሁን ችግር ሲገጥማችሁ ነው የምትፈልጉኝ?” አላቸው።

8. የገለዓድ አለቆችም፣ “እንግዲህ አሁን ወደ አንተ መጥተናል፤ አሞናውያንን እንድንወጋ በል ተነሥና አብረን እንሂድ፤ በገለዓድ በምንኖረው በሁላችንም ላይ አለቃ ትሆናለህ” አሉት።

9. ዮፍታሔም፣ “አሞናውያንን ለመውጋት ወደ አገሬ ብትመልሱኝና እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው በእርግጥ አለቃችሁ እሆናለሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

10. የገለዓድ አለቆችም፣ “እግዚአብሔር ምስክራችን ነው፤ ያልከውንም በእርግጥ እናደርጋለን” አሉት።

11. ስለዚህ ዮፍታሔ ከገለዓድ አለቆች ጋር ሄደ፤ ሕዝቡም በላያቸው ላይ አለቃና አዛዥ አደረጉት፤ ዮፍታሔም የተናገረውን ቃል ሁሉ ምጽጳ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ደገመው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 11