ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 1:22-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. የዮሴፍ ወገን ደግሞ ቤቴልን ወጉ፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነበር።

23. እነርሱም ቀደም ሲል ሎዛ ትባል ወደ ነበረችው ወደ ቤቴል ሰላዮችን በላኩ ጊዜ፣

24. ሰላዮቹም አንድ ሰው ከከተማዪቱ ሲወጣ አይተው፤ “የከተማዪቱን መግቢያ አሳየን፤ እኛም ምሕረት እናደርግልሃለን” አሉት።

25. እርሱም አሳያቸው፤ እነርሱም ከሰውየውና ከቤተ ሰቡ በስተቀር የከተማዪቱን ሕዝብ በሰይፍ ስለት ፈጁ።

26. ሰውየውም ወደ ኬጢያውያን ምድር ሄዶ ከተማ ሠራ፤ ስሟንም ሎዛ ብሎ ጠራት፤ እስከ ዛሬም የምትጠራው በዚሁ ስም ነው።

27. የምናሴ ነገድ ግን በቤትሳን፣ በታዕናክ፣ በዶር፣ በይብለዓም፣ በመጊዶንና በየአካባ ቢያቸው ያሉት መንደሮች ነዋሪውን ሕዝብ ስላላስወጡ፣ ከነዓናውያን ኑሮአቸውን በዚያው ለማድረግ ወሰኑ።

28. እስራኤላውያን በበረቱ ጊዜ ግን ከነዓናውያንን የጒልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው እንጂ ፈጽሞ አላስወጧቸውም።

29. እንደዚሁም የኤፍሬም ወገኖች በጌዝር የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ማስወጣት አልቻሉም፤ ስለዚህ ከነዓናውያን በመካከላቸው እዚያው መኖርን ቀጠሉ።

30. ዛብሎንም እንደዚሁ በቂድሮንና በነህሎል የነበሩትን በመካከለቸው የቀሩትን ከነዓናውያንን አላስወጣም፤ ነገር ግን የጒልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዳቸው።

31. አሴርም በዓኮ፣ በሲዶን፣ በአሕላብ፣ በአክዚብ፣ በሒልባ፣ በኣፌቅና በረአብ የሚኖሩትን አላስወጣም፤

32. በዚህ ምክንያት የአሴር ሕዝብ በምድሪቱ ካሉት ከነዓናውያን ጋር አብረው ኖሩ።

33. ንፍታሌምም በቤት ሳሚስና በቤትዓናት የሚኖሩትን አላስወጣም፤ ስለዚህ የንፍታሌም ነገድ በምድሪቱ ከሚኖሩት ከነዓናውያን ጋር አብረው ኖሩ፤ ይሁን እንጂ በቤት ሳሚስና በቤትዓናት የሚኖሩት ለእነርሱ የጒልበት ሥራ ተገደው ይሠሩ ነበር።

34. የዳን ነገድ በኰረብታማው ምድር ብቻ እንዲወሰን እንጂ ወደ ሜዳማው አገር እንዲወርድ አሞራውያን አልፈቀዱለትም።

35. አሞራውያንም በሔሬስ ተራራ፣ በኤሎንና በሸዓልቢም ኑሯቸውን ቀጠሉ፤ ይሁን እንጂ የዮሴፍ ወገን በበረታ ጊዜ ተገደው የጒልበት ሥራ ከመሥራት አላመለጡም።

36. የአሞራውያን ድንበር አቅራቢያም መተላለፊያ እስከ ሴላዕና ከዚያም የሚያልፍ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 1