ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 1:18-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ደግሞም የይሁዳ ሰዎች ጋዛ፣ አስቀሎና፣ አቃሮን የተባሉትን ከተሞች ከነግዛቶቻቸው ያዙ።

19. እግዚአብሔር ከይሁዳ ሰዎች ጋር ነበር፤ ስለዚህ ኰረብታማውን አገር ያዙ፤ ነገር ግን በረባዳው ምድር የሚኖሩት ሰዎች ከብረት የተሠሩ ሠረገሎች ስለ ነበሯቸው ከዚያ አሳደው ሊያስወጧቸው አልቻሉም።

20. ሙሴ ባዘዘው መሠረት ኬብሮን ለካሌብ ተሰጠች፤ እርሱም ሦስቱን የዔናቅ ልጆች ከውስጧ አሳደደ።

21. የብንያም ልጆች በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን ከዚያ ሊያስወጧቸው አልቻሉም፤ ስለዚህ ኢያቡሳውያን እስከ ዛሬ ድረስ ከብንያማውያንጋር በዚያ አብረው ይኖራሉ።

22. የዮሴፍ ወገን ደግሞ ቤቴልን ወጉ፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነበር።

23. እነርሱም ቀደም ሲል ሎዛ ትባል ወደ ነበረችው ወደ ቤቴል ሰላዮችን በላኩ ጊዜ፣

24. ሰላዮቹም አንድ ሰው ከከተማዪቱ ሲወጣ አይተው፤ “የከተማዪቱን መግቢያ አሳየን፤ እኛም ምሕረት እናደርግልሃለን” አሉት።

25. እርሱም አሳያቸው፤ እነርሱም ከሰውየውና ከቤተ ሰቡ በስተቀር የከተማዪቱን ሕዝብ በሰይፍ ስለት ፈጁ።

26. ሰውየውም ወደ ኬጢያውያን ምድር ሄዶ ከተማ ሠራ፤ ስሟንም ሎዛ ብሎ ጠራት፤ እስከ ዛሬም የምትጠራው በዚሁ ስም ነው።

27. የምናሴ ነገድ ግን በቤትሳን፣ በታዕናክ፣ በዶር፣ በይብለዓም፣ በመጊዶንና በየአካባ ቢያቸው ያሉት መንደሮች ነዋሪውን ሕዝብ ስላላስወጡ፣ ከነዓናውያን ኑሮአቸውን በዚያው ለማድረግ ወሰኑ።

28. እስራኤላውያን በበረቱ ጊዜ ግን ከነዓናውያንን የጒልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው እንጂ ፈጽሞ አላስወጧቸውም።

29. እንደዚሁም የኤፍሬም ወገኖች በጌዝር የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ማስወጣት አልቻሉም፤ ስለዚህ ከነዓናውያን በመካከላቸው እዚያው መኖርን ቀጠሉ።

30. ዛብሎንም እንደዚሁ በቂድሮንና በነህሎል የነበሩትን በመካከለቸው የቀሩትን ከነዓናውያንን አላስወጣም፤ ነገር ግን የጒልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዳቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 1