ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 1:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኢያሱ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን፣ “ከነዓናውያንን ለመውጋት ማን ቀድሞ ይውጣልን?” ብለው እግዚአብሔርን ጠየቁ።

2. እግዚአብሔርም፣ “ይሁዳ ቀድሞ ይውጣ፤ እነሆ ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ ሰጥቼዋለሁ” በማለት መለሰ።

3. የይሁዳም ሰዎች ወንድሞቻቸውን የስምዖንን ልጆች፣ “ከነዓናውያንን ለመውጋት ድርሻችን ወደ ሆነው ምድር አብረን እንውጣ፤ እኛም እንደዚሁ ድርሻችሁ ወደ ሆነው ምድር አብረናችሁ እንወጣለን” አሏቸው፤ ስለዚህም የስምዖን ሰዎች አብረዋቸው ሄዱ።

4. ይሁዳ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ላይ ወጣ፤ እግዚአብሔርም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ ቤዜቅ በተባለውም ስፍራ ዐሥር ሺህ ሰው ገደሉ።

5. በዚህም ኦዶኒቤዜቅን አግኝተው ተዋጉት፤ ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን ድል አደረጉ።

6. አዶኒቤዜቅም ከዚያ ሸሸ፤ እነርሱ ግን አሳደው ያዙት፤ የእጆቹንና የእግሮቹንም አውራ ጣቶች ቈረጡ።

7. ከዚያም አዶኒቤዜቅ፣ “የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣቶች የተቈረጡባቸው ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ ሥር የወደቀ ፍርፋሪ ይለቃቅሙ ነበር፤ አሁን ግን እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የፈጸምሁትን አመጣብኝ” አለ፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤ በዚያም ሞተ።

8. የይሁዳ ሰዎች ኢየሩሳሌምን ወግተው ያዟት፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ስለት መተው፣ በእሳት አቃጠሏት።

9. ከዚያም በኋላ የይሁዳ ሰዎች በኰረብታማው አገር፣ በኔጌብና በምዕራቡ ኮረብታ ግርጌ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ለመውጋት ወረዱ፤

10. ቀደም ሲል ቂርያት አርባቅ ተብላ በምትጠራው በኬብሮን በሚኖሩት ከነዓናውያን ላይ ዘመቱ፤ ሴሲንን፣ አኪመንንና ተላሚንን ድል አደረጉ።

11. ከዚያም ቀደም ሲል ቅርያትሤፍር ተብላ በምትጠራው በዳቤር በሚኖሩት ሰዎች ላይ ዘመቱ።

12. ካሌብም፣ “ቅርያት ሤፍርን ወግቶ ለሚይዛት ሰው ልጄን ዓክሳንን እድርለታለሁ” አለ።

13. በዚህ ጊዜ የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ከተማዪቱን ያዘ፤ ካሌብም ልጁን ዓክሳንን ዳረለት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 1