ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 48:8-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. “ይሁዳን ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የሚያዋስነው ምድር ለመባ የሚቀርብ ድርሻ ይሆናል፤ ስፋቱም ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ነው፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያለውም ርዝመቱ፣ ከነገዶቹ ድርሻ እንደ አንዱ ሆኖ፣ መቅደሱ በመካከሉ ይሆናል።

9. “ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት የዚህ መባ ርዝመት ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ሲሆን፣ ስፋቱ ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል።

10. ይህ ለካህናቱ የተቀደሰ ድርሻ ይሆናል፤ በሰሜን በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ፣ በምዕራብ በኩል ወርዱ ዐሥር ሺህ ክንድ በምሥራቅ በኩል ወርዱ ዐሥር ሺህ ክንድ ሲሆን በደቡብ በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፤ የእግዚአብሔርም መቅደስ በመካከሉ ይቆማል።

11. ይህም እስራኤላውያን በሳቱ ጊዜ፣ እንደ ሳቱት ሌዋውያን ሳይስቱ ለቀሩት፣ በታማኝነት ላገለገሉኝ ለተቀደሱት ካህናት ለሳዶቃውያን ይሆናል።

12. የሌዋውያንን ምድር ከሚያዋስነው፣ ከምድሪቱ ቅዱስ ድርሻ እጅግ የተቀደሰው ድርሻ ለእነርሱ ልዩ ስጦታ ይሆናል።

13. “ከካህናቱም ምድር ጐን ለጐን ሌዋውያኑ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመትና ዐሥር ሺህ ክንድ ወርድ ያለው ይዞታ ይኖራቸዋል፤ ጠቅላላ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ፣ ወርዱም ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል።

14. ከዚህ ላይ መሸጥ ወይም መለወጥ የለባቸውም። ይህ ከምድሪቱ ሁሉ ምርጥ ስለ ሆነ፣ ወደ ሌላ እጅ አይተላለፍም፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነውና።

15. “አምስት ሺህ ክንድ ወርድና ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመት ያለው የቀረው ቦታ ለከተማዪቱ የጋራ ጥቅም፣ ለቤት ሥራና ለከብት ማሰማሪያ ይውላል፤ ከተማዪቱም በመካከሉ ትሆናለች፤

16. የከተማዪቱም መጠን በሰሜን አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፣ በደቡብ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፣ በምሥራቅ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፣ የምዕራቡም እንዲሁ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል።

17. የከተማዪቱ ከብት ማሰማሪያ ቦታ፣ በሰሜን ሁለት መቶ አምሳ ክንድ፣ በደቡብ ሁለት መቶ አምሳ ክንድ፣ በምሥራቅ ሁለት መቶ አምሳ ክንድ፣ በምዕራብም ሁለት መቶ አምሳ ክንድ ይሆናል።

18. ከዚህ የሚቀረው፣ የተቀደሰውን ክፍል የሚያዋስነውና በተጓዳኝ ያለው ቦታ በምሥራቅ ዐሥር ሺህ ክንድ፣ በምዕራብ ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። ምርቱም ለከተማዪቱ ሠራተኞች ምግብ ይሆናል።

19. ምድሪቱን የሚያርሱ የከተማዪቱ ሠራተኞች ከሁሉም ነገዶች ይመጣሉ።

20. አጠቃላይ ይዞታው በአራቱም ማእዘን እኩል ሲሆን፣ እያንዳንዱ ማእዘን ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ነው፤ ከከተማዪቱ ድርሻ ጋር የተቀደሰውን ክፍል ልዩ መባ በማድረግ ታስቀምጣላችሁ።

21. “በተቀደሰው ድርሻና በከተማዪቱ ቦታ ግራና ቀኝ ያለው ቀሪ ቦታ፣ ለገዡ ይሆናል፤ ይህም ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ከሆነው ከተቀደሰው ቦታ አንሥቶ በምሥራቅ በኩል እስከ ምሥራቁ ወሰን ይዘልቃል፤ በምዕራቡም በኩል እንዲሁ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ከሆነው ይዞታ አንሥቶ እስከ ምዕራቡ ወሰን ይዘልቃል። የየነገዱ ድርሻ ከሆነውም መሬት ጐን ለጐን የሚሄዱት ቦታዎች የገዡ ይሆናሉ። የተቀደሰው ቦታና መቅደሱ በመካከላቸው ይሆናሉ።

22. ስለዚህ የሌዋውያኑ ይዞታና የከተማዪቱ ይዞታ ለገዡ በተሰጠው ቦታ መካከል ይሆናል፤ የገዡ ቦታም በይሁዳ ድንበርና በብንያም ድንበር መካከል ይሆናል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 48